የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 27:1-12

ሐዋርያት ሥራ 27:1-12 NASV

ወደ ኢጣሊያ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሌሎቹን እስረኞች የንጉሠ ነገሥቱ ክፍለ ጦር አባል ለሆነው፣ ዩልዮስ ለተባለ የመቶ አለቃ አስረከቧቸው። ከአድራሚጢስ ተነሥቶ በእስያ አውራጃ ባሕር ዳርቻ ላይ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው መርከብ ተሳፍረን የባሕር ጕዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ ይኖር የነበረው የመቄዶንያ ሰው፣ አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋራ ነበረ። በሚቀጥለው ቀን ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ ሄዶ ርዳታ እንዲቀበል ፈቀደለት። ከዚያም ተነሥተን በባሕር ተጓዝን፤ ነፋስ ከፊት ለፊት ስለ ገጠመን፣ የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን ዐለፍን። በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ አገር ሙራ የተባለ ቦታ ደረስን። ከዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን። ብዙ ቀን በዝግታ እየተጓዝን ቀኒዶስ አካባቢ በጭንቅ ደረስን፤ ነፋሱም ወደ ፊት እንዳንሄድ በከለከለን ጊዜ፣ በሰልሙና አጠገብ አድርገን በቀርጤስ ተተግነን ሄድን፤ ጥግ ጥጉንም ይዘን፣ በላሲያ ከተማ አጠገብ ወዳለው፣ “መልካም ወደብ” ወደ ተባለ ስፍራ በጭንቅ ደረስን። ብዙ ጊዜ ባክኖ፤ የጾሙ ጊዜ ስላለፈ በመርከብ መጓዙ አደገኛ ሆኖ ነበርና ጳውሎስ፣ “እናንተ ሰዎች፤ ጕዞው አደገኛ እንደሚሆን፣ በመርከቡና በጭነቱ እንዲሁም በእኛ በራሳችን ላይ እንኳ ትልቅ ጕዳት እንደሚደርስ ይታየኛል” ብሎ አስጠነቀቃቸው። የመቶ አለቃው ግን ከጳውሎስ ምክር ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት ያሉትን ይሰማ ነበር። ክረምቱንም በዚያ ለማሳለፍ ወደቡ አመቺ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ፍንቄ ወደተባለው ወደብ ደርሰው በዚያ ለመክረም ተስፋ በማድረግ ጕዟችንን እንድንቀጥል ውሳኔ አስተላለፉ፤ ወደቡም በቀርጤስ ደቡብ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትይዩ የሚገኝ ነበር።