የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 26:1-23

ሐዋርያት ሥራ 26:1-23 NASV

አግሪጳም ጳውሎስን፣ “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መከላከያውን አቀረበ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ አይሁድ በእኔ ላይ ላቀረቡት ክስ ሁሉ ዛሬ በፊትህ የመከላከያ መልስ ለማቅረብ በመቻሌ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቈጥረዋለሁ፤ ይኸውም አንተ በተለይ የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ ስለምታውቅ ነው፤ ስለዚህ በትዕግሥት እንድታደምጠኝ እለምንሃለሁ። “ገና ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በአገሬም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደ ኖርሁ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ ደግሞም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለሚያውቁኝ ከሃይማኖታችን እጅግ ጥብቅ በሆነው ወገን ውስጥ ሆኜ እንደ አንድ ፈሪሳዊ መኖሬን ሊመሰክሩ ፈቃደኞች ከሆኑ ቃላቸውን ሊሰጡ ይችላሉ። አሁንም ተከስሼ እዚህ የቀረብሁበት ምክንያት፣ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ቃል የገባውን ነገር ተስፋ በማድረጌ ነው። ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ከልብ እያገለገሉ፣ ሲፈጸም ለማየት የሚተጉለትም ተስፋ ይኸው ነው። ንጉሥ ሆይ፤ አይሁድም የሚከስሱኝ ስለዚሁ ተስፋ ነው። ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር ሙታንን ማስነሣት እንደማይችል አድርጋችሁ የምትቈጥሩት ለምንድን ነው? “እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም በምችለው መንገድ ሁሉ መቃወም እንዳለብኝ ወስኜ ነበር። በኢየሩሳሌምም ያደረግሁት ይህንኑ ነበር፤ ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብዬ ብዙ ቅዱሳንን አሳስሬአለሁ፤ በመገደላቸውም ተስማምቻለሁ፤ ላስቀጣቸውም ብዙ ጊዜ ከምኵራብ ምኵራብ እየተዘዋወርሁ፣ የስድብ ቃል እንዲናገሩ አስገድዳቸው ነበር፤ በቍጣም ተሞልቼ በውጭ አገር እስከሚገኙ ከተሞች ድረስ ተከታትዬ አሳደድኋቸው። “በዚህ መሠረት አንድ ቀን ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ በምጓዝበት ጊዜ፣ ንጉሥ ሆይ፤ እኩለ ቀን ላይ በመንገድ ሳለሁ፣ ብሩህነቱ ከፀሓይ የሚበልጥ ብርሃን በእኔና በባልንጀሮቼ ዙሪያ ከሰማይ ሲያበራ አየሁ፤ ሁላችንም በምድር ላይ ወደቅን፤ እኔም በዕብራይስጥ ቋንቋ፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን ብትጋፋ ጕዳቱ በአንተ ይብሳል’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ ” አልሁ። “ጌታም እንዲህ አለኝ፤ ‘እኔ፣ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። አሁንም፣ ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለ እኔ ስላየኸውና ወደ ፊትም ስለማሳይህ ነገር አገልጋይና ምስክር እንድትሆን ልሾምህ ተገልጬልሃለሁ። ከገዛ ሕዝብህና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ፤ አንተም ዐይናቸውን ትከፍታለህ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸዋለህ፤ እነርሱም የኀጢአትን ይቅርታ ይቀበላሉ፤ በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስት ያገኛሉ።’ “እንግዲህ፣ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ከሰማይ ለታየኝ ራእይ አልታዘዝ አላልሁም፤ ነገር ግን በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ። አይሁድም በመቅደስ ይዘው ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚሁ ምክንያት ነው። የእግዚአብሔር ርዳታ እስከ ዛሬ ስላልተለየኝ፣ እነሆ፤ እዚህ ቆሜ ለትንሹም ለትልቁም እመሰክራለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆናል፣ ይፈጸማል ካሉት በስተቀር አንዳች ነገር አልተናገርሁም፤ ይኸውም ክርስቶስ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብክ ነው።”