ከጥቂት ቀንም በኋላ፣ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን እጅ ሊነሡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጡ፤ ፊስጦስም የጳውሎስን ጕዳይ አንሥቶ ለንጉሡ እንዲህ አለው፤ “ፊልክስ በእስር ቤት የተወው አንድ ሰው እዚህ አለ፤ ወደ ኢየሩሳሌም በሄድሁ ጊዜ፣ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እንድፈርድበት ከስሰውት ነበር። “እኔም፣ ተከሳሽ በከሳሾቹ ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር መልስ ለመስጠት ዕድል ሳያገኝ፣ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ልማድ እንዳልሆነ ነገርኋቸው። ስለዚህ ከሳሾቹ ከእኔ ጋር ወደዚህ በመጡ ጊዜ፣ ጕዳዩን ሳላጓትት በማግስቱም ችሎት ተቀምጬ ያን ሰው እንዲያቀርቡት አዘዝሁ። ከሳሾቹም ተነሥተው በመቆም ሲናገሩ፣ እኔ ያሰብሁትን ያህል ከባድ ክስ አላቀረቡበትም፤ ይልቁን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ሞቶ ስለ ነበረው፣ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው፣ ስለ ኢየሱስ ይከራከሩት ነበር። እኔም ይህን ነገር እንዴት እንደምፈታው ግራ ስለ ገባኝ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ስለዚሁ ጕዳይ እንዲፋረድ ፈቃደኝነቱን ጠየቅሁት። ነገር ግን ጳውሎስ ጕዳዩ በንጉሠ ነገሥቱ እንዲታይለት ይግባኝ ባለ ጊዜ፣ እኔም ወደ ቄሳር እስከምልከው ድረስ እስር ቤት እንዲቈይ አዘዝሁ።” አግሪጳም ፊስጦስን፣ “እኔም እኮ ይህ ሰው ሲናገር መስማት እፈልግ ነበር” አለው። እርሱም፣ “እንግዲያውስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው። በማግስቱም አግሪጳና በርኒቄ በታላቅ ክብር መጥተው፣ ከከፍተኛ መኰንኖችና ከከተማዪቱ ታላላቅ ሰዎች ጋር ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ገቡ፤ በፊስጦስም ትእዛዝ ጳውሎስ እንዲቀርብ ተደረገ። በዚህ ጊዜ ፊስጦስ እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ እንዲሁም እዚህ አብራችሁን ያላችሁ ሁሉ፤ ይህን ሰው ታዩታላችሁ? በኢየሩሳሌምና እዚህ በቂሳርያም የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ፣ ይህ ሰው ከእንግዲህ በሕይወት መኖር አይገባውም በማለት እየጮኹ ለመኑ። እኔም ለሞት የሚያበቃ አንዳች ነገር አለማድረጉን ተረዳሁ፤ ሆኖም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ በማለቱ ወደ ሮም ልልከው ወሰንሁ። ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የተረጋገጠ ነገር አላገኘሁም፤ ስለዚህም ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር ለማግኘት በሁላችሁም ፊት፣ በተለይ ደግሞ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ በአንተ ፊት አቀረብሁት። ይኸውም አንድ እስረኛ ወደ በላይ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት አለመግለጽ ትክክል ስላልመሰለኝ ነው።”
ሐዋርያት ሥራ 25 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 25
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 25:13-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos