የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 24:1-16

ሐዋርያት ሥራ 24:1-16 NASV

ከአምስት ቀን በኋላ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከአንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጡለስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በጳውሎስም ላይ ያላቸውን ክስ ለአገረ ገዥው አቀረቡ። ጳውሎስ ተጠርቶ በቀረበ ጊዜ፣ ጠርጠሉስ እንዲህ ሲል ክሱን አቀረበ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ፤ በአንተ ዘመን ሰላም ለብዙ ጊዜ ሰፍኖልናል፤ አርቆ አስተዋይነትህም ለዚህ ሕዝብ መሻሻልን አስገኝቶለታል፤ በየቦታውና በየጊዜው ይህን ውለታ በታላቅ ምስጋና እንቀበላለን። ነገር ግን ይበልጥ እንዳላደክምህ፣ በዐጭሩ እንድትሰማን መልካም ፈቃድህን እለምንሃለሁ። “ይህ ሰው፣ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ መካከል በሽታ ሆኖ ሁከት የሚያስነሣ፣ ደግሞም የናዝራውያን ወገን ቀንደኛ መሪ ሆኖ አግኝተነዋል። ከዚህም በላይ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር አግኝተን ያዝነው። በሕጋችንም መሠረት ልንፈርድበት አስበን ነበር፤ ነገር ግን የጦር አዛዡ ሉስዮስ መጥቶ በታላቅ ኀይል ከእጃችን ነጥቆ ወሰደው፤ ከሳሾቹም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዘ። እንግዲህ አንተ ራስህ መርምረኸው እርሱን የከሰስንበትን ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን ልታረጋግጥ ትችላለህ።” አይሁድም ነገሩ እንደ ተባለው መሆኑን በመደገፍ በክሱ ተባበሩ። አገረ ገዥውም እንዲናገር በእጁ ምልክት በሰጠው ጊዜ፣ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ የዚህ ሕዝብ ፈራጅ መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ የመከላከያ መልሴን የማቀርበው በደስታ ነው። ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም የመጣሁት ከዐሥራ ሁለት ቀን በፊት መሆኑን አንተው ራስህ በቀላሉ ማረጋገጥ ትችላለህ። ከሳሾቼም በቤተ መቅደስ ከማንም ጋር ስከራከር ወይም በምኵራብ ወይም በከተማ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ሕዝብን ሳነሣሣ አላገኙኝም። አሁንም ለተከሰስሁበት ነገር ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። ይሁን እንጂ፣ እነርሱ ኑፋቄ በሚሉት በጌታ መንገድ የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ፤ በሕጉ የታዘዘውንና በነቢያት የተጻፈውን ሁሉ አምናለሁ፤ ደግሞም እንደነዚህ ሰዎች ሁሉ፣ ጻድቃንና ኀጥኣን ከሙታን እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አለኝ። ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ሁልጊዜ እጥራለሁ።