የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 22:1-21

ሐዋርያት ሥራ 22:1-21 NASV

“ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አሁን የማቀርብላችሁን የመከላከያ መልሴን ስሙኝ።” እነርሱም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ፣ ከፊት ይልቅ ጸጥ አሉ። ጳውሎስም እንዲህ አለ፤ “እኔ በኪልቅያ በምትገኘው በጠርሴስ የተወለድሁ አይሁዳዊ ስሆን፣ ያደግሁት ግን በዚህ ከተማ ነው። የአባቶቻችንን ሕግ በገማልያል እግር ሥር ተቀምጬ በሚገባ ተምሬአለሁ፤ ዛሬ እናንተ እንዲህ የምትቀኑለትን ያህል እኔም ለእግዚአብሔር እቀና ነበር። ይህን መንገድ የሚከተሉትንም እስከ ሞት ድረስ እያሳደድሁ፣ ወንዶችንም ሴቶችንም አስሬ ወደ ወህኒ እጥላቸው ነበር። ይህን ተግባሬን ሊቀ ካህናቱም ሆነ ሸንጎው ሁሉ ሊመሰክሩ ይችላሉ። ከእነርሱ ደብዳቤ ተቀብዬ ደማስቆ ወዳሉት ወንድሞቻቸው በመሄድ፣ እነዚህን ሰዎች አሳስሬ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥቼ ለማስቀጣት ወደዚያ እሄድ ነበር። “ስንጓዝም እኩለ ቀን ገደማ ወደ ደማስቆ እንደ ተቃረብሁ፣ ድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ በራ፤ እኔም ምድር ላይ ወደቅሁ፤ ከዚያም፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ አልሁት። “እርሱም፣ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ። ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አዩ፤ ነገር ግን የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ በትክክል አልሰሙም። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ምን ላድርግ?’ አልሁት። “ጌታም፣ ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ሁሉ ይነግሩሃል’ አለኝ። ከብርሃኑም ጸዳል የተነሣ ዐይኔ ስለ ታወረ፣ ከእኔ ጋር የነበሩት እጄን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አደረሱኝ። “ከዚያም ሐናንያ የተባለ ሰው ሊያየኝ ወደ እኔ መጣ፤ እርሱም ሕግን በጥንቃቄ የሚጠብቅና በዚያ በሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ነበረ። በአጠገቤም ቆሞ፣ ‘ወንድም ሳውል ሆይ፤ ዐይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ፤ እኔም በዚያችው ቅጽበት አየሁት። “እርሱም ቀጥሎ እንዲህ አለ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና ቃሉን ከአንደበቱ እንድትሰማ መርጦሃል፤ ስላየኸውና ስለ ሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆነዋለህና። ታዲያ፣ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነሥተህ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’ “ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ በቤተ መቅደስ ስጸልይም ተመሰጥሁ፤ ጌታም ሲናገረኝ አየሁ፤ እርሱም አሁኑኑ፣ ‘ፈጥነህ ከኢየሩሳሌም ውጣ! ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና’ አለኝ። “እኔም እንዲህ አልሁት፤ ‘ጌታ ሆይ፤ በአንተ የሚያምኑትን ሰዎች ለማሰርና ለመደብደብ፣ በየምኵራቡ ስዞር እንደ ነበር እነዚህ ሰዎች ያውቃሉ፤ ደግሞም የአንተን ሰማዕት የእስጢፋኖስን ደም በሚያፈስሱበት ጊዜ፣ በድርጊታቸው ተስማምቼ በቦታው ቆሜ የገዳዮቹን ልብስ እጠብቅ ነበር።’ “ጌታም፣ ‘ሂድ፤ በሩቅ ወዳሉት አሕዛብ እልክሃለሁና’ አለኝ።”