ሐዋርያት ሥራ 20:1-16

ሐዋርያት ሥራ 20:1-16 NASV

ሁከቱም እንደ በረደ፣ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርትን አስጠርቶ መከራቸው፤ ተሰናብቷቸውም ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ተነሣ። ባለፈባቸውም ስፍራዎች ሕዝቡን በብዙ ቃል እየመከረ ግሪክ አገር ደረሰ፤ በዚያም ሦስት ወር ተቀመጠ። ወደ ሶርያ በመርከብ ለመሄድ ሲዘጋጅም አይሁድ አሢረውበት ስለ ነበር፣ በመቄዶንያ በኩል አድርጎ ለመመለስ ወሰነ። የጳይሮስ ልጅ የቤርያው ሱሲጴጥሮስ፣ የተሰሎንቄዎቹ አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ፣ የደርቤኑ ጋይዮስ፣ ከእስያ አውራጃ የመጡት ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ እንዲሁም ጢሞቴዎስ ዐብረውት ሄዱ። እነዚህም ሰዎች ወደ ፊት ቀድመውን በጢሮአዳ ጠበቁን። እኛ ግን የቂጣ በዓል ካለፈ በኋላ፣ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሣን፤ ከዐምስት ቀንም በኋላ ከሌሎቹ ጋራ በጢሮአዳ ተገናኘን፤ በዚያም ሰባት ቀን ተቀመጥን። በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቍረስ ተሰብስበን ሳለን፣ ጳውሎስ በማግስቱም ለመሄድ ስላሰበ፣ ከእነርሱ ጋራ ይነጋገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አራዘመ። በተሰበሰብንበትም ሰገነት ላይ ብዙ መብራት ነበር። አውጤኪስ የተባለ አንድ ጐበዝም በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ አለውና ጭልጥ ብሎ ተኛ፤ ከሦስተኛውም ፎቅ ቍልቍል ወደቀ፤ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ተጋድሞ ዐቀፈውና፣ “ሕይወቱ በውስጡ ስላለች ሁከት አትፍጠሩ!” አላቸው። ተመልሶም እንደ ገና ወደ ፎቁ ወጣ፤ እንጀራውንም ቈርሶ በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ብዙ ከተናገረ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። ሰዎችም ያን ጐበዝ ሕያው ሆኖ ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ። እኛ ግን ጳውሎስን ለመቀበል ቀድመን ወደ መርከቡ ሄድን፤ ከዚያም በመርከብ ወደ አሶን ተጓዝን፤ ይህን ያደረግነውም ጳውሎስ በየብስ በእግሩ ሊሄድ ስላሰበ ነበር። በአሶን ከተገናኘንም በኋላ፣ ተቀብለነው ዐብረን በመርከብ ወደ ሚጢሊኒ ሄድን። በማግስቱም በመርከብ ተጕዘን ከኪዩ ደሴት ትይዩ ደረስን። በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞን ተሻገርን፤ በማግስቱም ሚሊጢን ደረስን። ጳውሎስም በእስያ አውራጃ ብዙ መቈየት ስላልፈለገ፣ ወደ ኤፌሶን ሳይገባ ዐልፎ ለመሄድ ወሰነ፤ ቢቻል በዓለ ዐምሳን በኢየሩሳሌም ለመዋል ቸኵሎ ነበርና።