አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ፣ ጳውሎስ በላይኛው አገር ዐልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አግኝቶ፣ “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፣ “አልተቀበልንም፤ እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ አልሰማንም” አሉት። ጳውሎስም፣ “ታዲያ፣ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት። ጳውሎስም፣ “የዮሐንስ ጥምቀትማ የንስሓ ጥምቀት ነበር፤ ዮሐንስም ራሱ ሰዎች ከርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ እንዲያምኑ ተናግሯል” አላቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያህል ነበሩ። ጳውሎስም ወደ ምኵራብ እየገባ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያሳመናቸው ሦስት ወር ሙሉ ምንም ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር። አንዳንዶቹ ግን ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የጌታንም መንገድ በገሃድ ያጥላሉ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ትቷቸው ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያነጋግራቸው ነበር። ይህን ማድረጉንም ሁለት ዓመት ስለ ቀጠለ፣ በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ። እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤ መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቅቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር። እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዝዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኩሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤ የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር። ርኩስ መንፈሱም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?” አላቸው። ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘልሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቍታቸውን ሸሹ። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ። ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጽ ተናዘዙ፤ ሲጠነቍሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ ዐምሳ ሺሕ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ። በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።
ሐዋርያት ሥራ 19 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 19
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 19:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች