የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 16:6-15

ሐዋርያት ሥራ 16:6-15 NASV

ጳውሎስና ባልደረቦቹ ቃሉን በእስያ እንዳይሰብኩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ አገር ዐልፈው ሄዱ። ወደ ሚስያም በተቃረቡ ጊዜ፣ ወደ ቢታኒያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም። ስለዚህ በሚስያ በኩል አድርገው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ። ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወንጌልን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል ብለን በመወሰን ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን። ከጢሮአዳ በመርከብ ተነሥተን በቀጥታ ተጕዘን ወደ ሳሞትራቄ መጣን፤ በማግስቱም ጕዟችንን ወደ ናጱሌ ቀጠልን፤ ከዚያም የሮማውያን ቅኝና የአካባቢው የመቄዶንያ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ገባን፤ በዚያም አያሌ ቀን ተቀመጥን። በሰንበት ቀንም፣ የጸሎት ስፍራ በመፈለግ፣ ከከተማዪቱ በር ወጥተን ወደ አንድ ወንዝ ወረድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን። ከሚያዳምጡትም ሴቶች መካከል ልድያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ነበረች። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ ልቧን ከፈተላት። እርሷና ቤተ ሰዎቿ ከተጠመቁ በኋላም፣ “በጌታ ማመኔን በርግጥ ከተረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ መጥታችሁ ጥቂት ተቀመጡ” በማለት አጥብቃ ለመነችን።