የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 11:19-30

ሐዋርያት ሥራ 11:19-30 NASV

በእስጢፋኖስ ላይ በተነሣው ስደት ምክንያት የተበተኑት አማኞች ቃሉን ለአይሁድ ብቻ እየተናገሩ እስከ ፊንቄ፣ እስከ ቆጵሮስና እስከ አንጾኪያ ድረስ ዘለቁ። ከቆጵሮስና ከቀሬና የመጡት አንዳንዶች ሰዎች ግን ወደ አንጾኪያ ሄደው ለግሪኮችም ጭምር በመንገር የጌታን የኢየሱስን ወንጌል ሰበኩላቸው። የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋራ ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ተመለሱ። ወሬውም በኢየሩሳሌም ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን ጆሮ ደረሰ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም በርናባስን ወደ አንጾኪያ ላከችው። እርሱም እዚያ ደርሶ እግዚአብሔር በጸጋው የሠራውን ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉም በፍጹም ልብ በጌታ በመታመን እንዲጸኑ መከራቸው። እርሱም መንፈስ ቅዱስንና እምነትን የተሞላ ደግ ሰው ነበር፤ ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመረ። ከዚህ በኋላ በርናባስ፣ ሳውልን ለመፈለግ ወደ ጠርሴስ ሄደ፤ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። ሁለቱም እዚያ ካለችው ቤተ ክርስቲያን ጋራ በመሆን አንድ ዓመት ሙሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያን” ተብለው ተጠሩ። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ። ከእነርሱም አንዱ አጋቦስ የተባለው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ እንደሚሆን መንፈስ ቅዱስ አስመልክቶት ተናገረ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሳር ዘመን ተፈጸመ። ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው ዐቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ የሚኖሩትን ወንድሞች ለመርዳት ወሰኑ፤ ርዳታውንም በበርናባስና በሳውል እጅ ለሽማግሌዎቹ በመላክ፣ ይህንኑ አደረጉ።