ሐዋርያት ሥራ 10:34-48

ሐዋርያት ሥራ 10:34-48 NASV

ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእውነት ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል። እግዚአብሔር፣ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እስራኤል ሕዝብ የላከውም የሰላም የምሥራች መልእክት ይኸው ነው። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በመላው ይሁዳ የሆነውን ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ። “እርሱ በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ላደረገው ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ ደግሞም ሰዎች እርሱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሣው፤ እንዲታይም አደረገው፤ የታየውም ለሁሉ ሰው ሳይሆን፣ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ዐብረነው ለበላንና ለጠጣን፣ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለመረጠን ለእኛ ለምስክሮቹ ነው። ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን እንድንመሰክር እርሱ ራሱ አዘዘን፤ በርሱም የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ስርየት እንደሚቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” ጴጥሮስ ይህን እየተናገረ ሳለ፣ ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። ከጴጥሮስ ጋራ የመጡት፣ ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ ተገረሙ። ይኸውም በልሳን ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ስለ ሰሟቸው ነው። በዚያ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፤ “እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉ፣ እንግዲህ በውሃ እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው ማን ነው?” ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ፣ ጴጥሮስ ጥቂት ቀን ከእነርሱ ጋራ እንዲቀመጥ ለመኑት።