ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው፤ በቍጥጥሩም ሥር አዋላቸው፤ ሜቴግ አማ የተባለችውንም ከተማ ከፍልስጥኤማውያን ቍጥጥር ነጻ አደረጋት። እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረገ፤ በመሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው፤ በገመድ ከተለኩትም ሁለት እጅ ሲገድል፣ አንድ እጅ ግን በሕይወት ይተው ነበር። ስለዚህ ሞዓባውያን የዳዊት ተገዦች ሆኑ፤ ገበሩለትም። ከዚህም በቀር ዳዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ፣ የሱባን ንጉሥ የረአብን ልጅ አድርአዛርን ወጋው። ዳዊትም አንድ ሺሕ ሠረገሎች፣ ሰባት ሺሕ ፈረሰኞችና ሃያ ሺሕ እግረኞች ማረከበት። ቍጥራቸው መቶ የሆነ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቈረጠ። የደማስቆዎቹ ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ሃያ ሁለት ሺሕ ሰው ገደለባቸው። ከዚያም የደማስቆ ክፍል በሆነው የሶርያውያን ግዛት የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ሶርያውያን ተገዙለት፤ ገበሩለትም። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው። ዳዊት የአድርአዛር ሹማምት ያነገቧቸውን የወርቅ ጋሻዎች ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸው። ንጉሡ ዳዊት ቤጣህና ቤሮታይ ከተባሉ ከአድርአዛር ከተሞችም እጅግ ብዙ ናስ አጋዘ። የሐማት ንጉሥ ቶዑ፣ ዳዊት መላውን የአድርአዛርን ሰራዊት ማሸነፉን በሰማ ጊዜ፣ ቶዑ ከአድርአዛር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ስለ ነበር፣ ሰላምታና በአድርአዛር ላይ ስለ ተቀዳጀውም ድል የደስታ መግለጫ እንዲያቀርብለት፣ ልጁን ዮራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የብር፣ የወርቅና የናስ ዕቃ ይዞ መጣ። ንጉሥ ዳዊትም፣ ቀድሞ ካስገበራቸው መንግሥታት ሁሉ በገባለት ብርና ወርቅ እንዳደረገው፣ እነዚህንም ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ቀደሳቸው። የገበሩትም መንግሥታት ኤዶምና ሞዓብ፣ አሞናውያን፣ ፍልስጥኤማውያንና አማሌቃውያን ነበሩ። እንዲሁም ከሱባ ንጉሥ ከረአብ ልጅ ከአድርአዛር የወሰደውን ምርኮ ለእግዚአብሔር ቀደሰ። ዳዊት የጨው ሸለቆ በተባለው ስፍራ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ኤዶማውያንን ገድሎ ከተመለሰ በኋላ ስሙ ገነነ። በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ኤዶማውያን ሁሉ ለዳዊት ተገዙ፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን ሰጠው። ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍትሕና ርትዕ አሰፈነላቸው። የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የሰራዊቱ አለቃ ሲሆን፣ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥም ታሪክ ጸሓፊ ነበረ። እንዲሁም የአኪጦብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቢሜሌክ ካህናት ሲሆኑ፣ ሠራያ ጸሓፊ ነበረ፤ የዮዳሔ ልጅ በናያስ የከሪታውያንና የፈሊታውያን አለቃ ሲሆን፣ የዳዊት ወንዶች ልጆች ደግሞ የቤተ መንግሥት አማካሪዎች ነበሩ።
2 ሳሙኤል 8 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ሳሙኤል 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ሳሙኤል 8:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos