የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ሳሙኤል 7:1-16

2 ሳሙኤል 7:1-16 NASV

ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣ ነቢዩን ናታንን፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው። ናታንም፣ “እግዚአብሔር ካንተ ጋር ስለሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው። በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፤ “ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤ እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። ከእስራኤላውያን ሁሉ ጋር በተጓዝሁበት ስፍራ ሁሉ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲጠብቁ ካዘዝኋቸው መሪዎቻቸው አንዱን፣ “ከዝግባ ዕንጨት ለምን ቤት አልሠራህልኝም?” ያልሁት አለን?’ “አሁንም ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፤ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ገዥ እንድትሆን ከሜዳ አነሣሁህ፤ ከበግ ጥበቃም ወሰድሁህ፤ በሄድህበት ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስማቸው በምድር ላይ ከገነነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እንደ አንዱ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ የራሱ የሆነ መኖሪያ እንዲኖረውና ከእንግዲህ ወዲያ እንዳይናወጥ፣ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጠዋለሁ፤ አጸናዋለሁም። ከዚህ በፊት እንደ ሆነውም ከእንግዲህ ወዲህ ክፉ ሕዝብ አይጨቍነውም፤ ለሕዝቤ ለእስራኤልም መሪዎች ከሾምሁለት ጊዜ አንሥቶ እንዳደረጉበት ሁሉ ከእንግዲህ አያደርጉበትም፤ እንዲሁም ከጠላቶችህ ሁሉ እጠብቅሃለሁ። “ ‘እግዚአብሔር ራሱ ቤት እንደሚሠራልህ ይነግርሃል፤ ዕድሜህን ጨርሰህ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ፣ በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። ለስሜ ቤት የሚሠራ እርሱ ነው፤ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ። አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል። በደል ቢፈጽም ግን ሰዎች በሚቀጡበት በትር እቀጣዋለሁ፤ የሰው ልጆችም በዐለንጋ እንደሚገረፉ እገርፈዋለሁ። ምሕረቴን ከአንተ በፊት ካስወገድሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ሁሉ ከእርሱ አላርቅም። ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።’ ”