2 ሳሙኤል 6:1-15
2 ሳሙኤል 6:1-15 NASV
ዳዊት እንደ ገና ከእስራኤል የተመረጡ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺሕ ሰዎች ሰበሰበ። እርሱና ዐብረውት ያሉት ሰዎች ሁሉ በታቦቱ ላይ ባለው ኪሩቤል ላይ በተቀመጠው በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ወደ ባኣላ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው፣ በኰረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም የአሚናዳብ ልጆች ዖዛና አሒዮ ሲሆኑ፣ የእግዚአብሔርም ታቦት በሠረገላው ላይ ሆኖ፣ አሒዮ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጸናጽልና በቃጭል ባለ ኀይላቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽቡ ነበር። ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለ ተደናቀፉ፣ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ። የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛንን ስለ ሰበረው፣ ዳዊት ተከፋ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፔሬዝ ዖዛ ተብሎ ይጠራል። ዳዊት በዚያ ቀን እግዚአብሔርን ስለ ፈራ “የእግዚአብሔር ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ። ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት ዐብሮት እንዲሆን ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈለገም፤ በዚህ ፈንታ አቅጣጫ ለውጦ የጋት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው። የእግዚአብሔርም ታቦት የጋት ሰው በሆነው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤተ ሰቡን ሁሉ ባረከ። በዚህ ጊዜ፣ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የአቢዳራን ቤተ ሰውና ያለውን ሁሉ እግዚአብሔር ባረከለት” ብለው ለንጉሥ ዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያው ወርዶ፣ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ አመጣው። እነዚያ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ስድስት ርምጃ በሄዱ ቍጥር፣ አንድ በሬና አንድ የሠባ ጥጃ ይሠዋ ነበር። ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ በወገቡ ታጥቆ በሙሉ ኀይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይጨፍር ነበር። እንዲህ ባለ ሁኔታም ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት ሆይ እያሉና ቀንደ መለከቱን እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ።

