የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ሳሙኤል 5:1-16

2 ሳሙኤል 5:1-16 NASV

የእስራኤል ነገዶች በሙሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ እኛ የዐጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ ባለፈው ሳኦል በእኛ ላይ ነግሦ በነበረ ጊዜ፣ እስራኤልን በጦርነት የምትመራቸው አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፤ መሪያቸውም ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።” ስለዚህም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም ኬብሮን ላይ በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እነርሱም ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት። ዳዊት በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ አርባ ዓመትም ገዛ። በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር፣ ኢየሩሳሌም ሆኖም በመላው እስራኤልና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። ንጉሡና ሰዎቹ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ለመውጋት ወደዚያ ሄዱ። ኢያቡሳውያንም፣ “ዳዊት እዚህ ሊገባ አይችልም” ብለው ስላሰቡ ዳዊትን፣ “ዕውሮችና ዐንካሶች እንኳ ይከለክሉሃልና ወደዚህች አትገባም” አሉት። ይሁን እንጂ ዳዊት የጽዮንን ዐምባ ያዘ፤ ይህችም የዳዊት ከተማ የተባለችው ናት። በዚያም ዕለት ዳዊት፣ “ኢያቡሳውያንን ድል ማድረግ የሚፈልግ፣ የዳዊት ጠላቶች ወደሚሆኑ፣ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ለመድረስ በውሃ መተላለፊያው ሽቅብ መውጣት አለበት” አለ። እንግዲህ፣ “ ‘ዐንካሶችና ዕውሮች’ ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም” ያሉት ለዚህ ነው። ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ላይ አደረገ፤ የዳዊት ከተማም ብሎ ጠራት። ዳዊትም ከሚሎ አንሥቶ ወደ ውስጥ ዙሪያዋን ገነባት። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ ዳዊት ከዕለት ወደ ዕለት እየበረታ ሄደ። በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ እንዲሁም የዝግባ ዕንጨት፣ ዐናጢዎችንና ድንጋይ ጠራቢዎችን አብሮ ሰደደ፤ እነርሱም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ሠሩለት። እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥነቱን እንዳጸናለት፣ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን እንዳሰፋለት ዳዊት ዐወቀ። ዳዊት ከኬብሮን ከሄደ በኋላ፣ ከበፊቶቹ በተጨማሪ በኢየሩሳሌም ሌሎች ቁባቶች አስቀመጠ፤ ሚስቶችም አገባ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት። በኢየሩሳሌም የተወለዱለትም ልጆች ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ናፌቅ፣ ናፍያ፣ ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት ይባላሉ።