2 ሳሙኤል 18
18
የአቤሴሎም መሞት
1ዳዊት አብሮት የነበረውን ሕዝብ ቈጠረ፤ የሻለቆችንና የመቶ አለቆችን ሾመላቸው። 2ዳዊትም ሰራዊቱን ሲሦውን በኢዮአብ፣ ሲሦውን በኢዮአብ ወንድም በጽሩያ ልጅ በአቢሳ፣ ሲሦውን ደግሞ በጌታዊው በኢታይ አዛዥነት ሥር ላካቸው። ንጉሡም ለሰራዊቱ፣ “እኔ ራሴም አብሬአችሁ በርግጥ እወጣለሁ” አላቸው።
3ሰዎቹ ግን፣ “አንተ መውጣት የለብህም፤ እንድንሸሽ ብንገደድ፣ ሰዎቹ ከቁም ነገር አይቈጥሩንም፤ ግማሾቻችን እንኳ ብንሞት ደንታቸው አይደለም፣ አንተ ግን ብቻህን ከእኛ ከዐሥሩ ሺሕ ትበልጣለህ#18፥3 ሁለት የዕብራይስጥ ቅጆች፣ አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች እንዲሁም ቩልጌት ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ትርጕሞች ግን፣ አሁን እንደኛ የሆኑ ዐሥር ሺሕ አሉ ይላል።፤ ስለዚህ በከተማ ሆነህ ብትረዳን ይሻላል” አሉት።
4ንጉሡም፣ “መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ በመቶና በሺሕ እየሆነ ተሰልፎ ሲወጣ፣ ንጉሡ በቅጥሩ በር ቆሞ ነበር። 5ንጉሡም ኢዮአብን፣ አቢሳንና ኢታይን፣ “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ ልጄ በአቤሴሎም ላይ ጕዳት እንዳታደርሱበት” ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡ ልጁን አቤሴሎምን አስመልክቶ ለእያንዳንዱ አዛዥ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰራዊቱ ሁሉ ሰማ።
6ሰራዊቱ እስራኤልን ለመውጋት ተሰልፎ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ጦርነቱም በኤፍሬም ደን ውስጥ ሆነ። 7እዚያም የእስራኤል ሰራዊት በዳዊት ሰዎች ተመታ፤ በዚያም ቀን ታላቅ ዕልቂት ሆነ፤ ሃያ ሺሕም ሰው ተገደለ። 8ውጊያው በገጠሩ ሁሉ ተስፋፋ፤ በዚያን ቀን ሰይፍ ከጨረሰው ይልቅ ጫካ ውጦ ያስቀረው ሰው በለጠ።
9በዚህ ጊዜ አቤሴሎም ከዳዊት ሰዎች ጋር ድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎም በበቅሎ ተቀምጦ ይሄድ ስለ ነበር፣ በቅሎዋ ጥቅጥቅ ያለ ቅርንጫፍ ባለው ትልቅ ወርካ ሥር በምታልፍበት ጊዜ፣ የአቤሴሎም ራስ በዛፉ ቅርንጫፍ ተያዘ፤ የተቀመጠበትም በቅሎ በሥሩ ስታልፍ፣ እርሱ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠልጥሎ ቀረ።
10አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮአብ፣ “እነሆ፤ አቤሴሎም በባሉጥ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት” አለው።
11ኢዮአብም ይህን የነገረውን ሰው፣ “ምን አልህ! ካየኸው ታዲያ ለምንድን ነው ያኔውኑ መትተህ መሬት ላይ ያልጣልኸው? ይህን አድርገህ ቢሆን ኖሮ፣ ዐሥር ሰቅል#18፥11 115 ግራም ያህል ነው። ጥሬ ብርና የጀግና ሰው ቀበቶም እሸልምህ ነበር” አለው።
12ሰውየው ግን እንዲህ አለ፤ “እኛ እየሰማን ንጉሡ፣ ‘ወጣቱ አቤሴሎም ጕዳት እንዳያገኘው ስለ እኔ ብላችሁ ጠብቁት’#18፥12 አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ የሰብዓ ሊቃናት፣ የቩልጌትና የሱርስት ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ አብዛኞቹን የዕብራይስጥ ቅጆች ግን፣ አቤሴሎም ምንም ዐይነት ሰው ቢሆን ይላሉ። ብሎ አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ያዘዛችሁ ስለሆነ፣ አንድ ሺሕ ሰቅል#18፥12 11 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ጥሬ ብር በእጄ ላይ ቢመዘንልኝ እንኳ፣ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሣም። 13በሌላ በኩል ደግሞ በነፍሴ ቈርጬ ሕይወቱን ባጠፋው ኖሮ#18፥13 ወይም፣ ወይም እርሱን ባታልለው ኖሮ፣ ከንጉሡ ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ፣ አንተም ራስህ አትቀርበኝም ነበር” ብሎ መለሰለት።
14ኢዮአብም፣ “ከእንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከአንተ ጋር ጊዜ ማጥፋት አልችልም” አለው፤ ስለዚህ በእጁ ሦስት ጦር ይዞ ሄደና አቤሴሎም እዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ፣ ወርውሮ በልቡ ላይ ተከላቸው። 15እንዲሁም ከኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ዐሥሩ አቤሴሎምን በመክበብ ወግተው ገደሉት።
16ከዚያም ኢዮአብ ቀንደ መለከት ነፍቶ ስለ ከለከላቸው፣ ሰራዊቱ እስራኤልን ማሳደዱን አቆመ። 17አቤሴሎምን ጫካ ወስደው በትልቅ ጕድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት፤ በላዩም ትልልቅ ድንጋይ ከመሩበት። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ወደየቤታቸው ሸሹ።
18አቤሴሎም፣ “ስሜን የሚያስጠራ ልጅ የለኝም” በማለት መታሰቢያ እንዲሆነው በሕይወት እያለ የንጉሥ ሸለቆ በተባለው ስፍራ በራሱ ስም ሐውልት አቁሞ ስለ ነበር፣ እስከ ዛሬ ድረስ የአቤሴሎም ሐውልት ተብሎ ይጠራል።
የዳዊት ሐዘን
19በዚህ ጊዜ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ፣ “እግዚአብሔር ጠላቶቹን የተበቀለለት መሆኑን ሮጬ ሄጄ ለንጉሡ የምሥራች ልንገረው” አለ።
20ኢዮአብም፣ “ዛሬ የምሥራቹን ወሬ የምትወስድለት አንተ አይደለህም፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ፣ ዛሬ ሳይሆን፣ የምሥራቹን ሌላ ጊዜ ታደርስለታለህ” አለው።
21ከዚያም ኢዮአብ ለኢትዮጵያዊው፣ “ሂድና ያየኸውን ለንጉሡ ንገር” አለው፤ ኢትዮጵያዊውም ኢዮአብን እጅ ነሥቶ እየሮጠ ሄደ።
22የሳዶቅ ልጅ አኪማአስም እንደ ገና ኢዮአብን፣ “የመጣው ይምጣ፤ እባክህ ኢትዮጵያዊውን ተከትየው ልሩጥ” አለው።
ኢዮአብ ግን፣ “ልጄ ሆይ፣ መሄድ ለምን አስፈለገህ? ሽልማት የሚያሰጥህ ምን የምሥራች ይዘህ ነው?” ብሎ መለሰለት።
23አኪማአስም፣ “የመጣው ይምጣ፤ መሄድ እፈልጋለሁ” አለ።
ስለዚህም ኢዮአብ፣ “እንግዲያውማ ሩጥ!” አለው። ከዚያም አኪማአስ በሜዳው መንገድ#18፥23 ይህ የዮርዳኖስ ሜዳማ ስፍራ ነው። ሮጦ ኢትዮጵያዊውን ቀድሞት ሄደ።
24ዳዊት በውስጠኛውና በውጭኛው በሮች መካከል ተቀምጦ ሳለ፣ ጠባቂው ቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ጣራ ወጥቶ ወደ ውጭ ሲመለከት፣ አንድ ሰው ብቻውን ሲሮጥ አየ። 25ጠባቂውም ተጣራና ይህንኑ ለንጉሡ ነገረው፤
ንጉሡም፣ “ብቻውን ከሆነ መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። ሰውየውም እየቀረበ መጣ።
26ከዚያም ጠባቂው ሌላ ሰው ሲሮጥ አይቶ፣ ዘበኛውን ተጣራና፣ “እነሆ ሌላም ሰው ብቻውን እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለ።
ንጉሡም፣ “ይኸኛውም መልካም ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ።
27ጠባቂውም፣ “የመጀመሪያው ሰው ሩጫ የሳዶቅን ልጅ የአኪማአስን ሩጫ ይመስለኛል” አለ።
ንጉሡም፣ “እርሱማ ጥሩ ሰው ነው፤ የምሥራች ሳይዝ አይመጣም” አለ።
28አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን፣ “ሁሉም ነገር ተሳክቷል” አለ፤ ከዚያም ወደ መሬት ለጥ ብሎ በንጉሡ ፊት እጅ ነሣና፣ “በጌታዬ በንጉሡ ላይ እጃቸውን ያነሡትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!” አለ።
29ንጉሡም፣ “ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን?” ሲል ጠየቀ።
አኪማአስም፣ “ኢዮአብ የንጉሡን አገልጋይና እኔንም ባሪያህን ሊልክ ሲል፣ ትልቅ ሁካታ አይቻለሁ፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቅሁም” ብሎ መለሰ።
30ንጉሡም፣ “ዕልፍ በልና ቁም” አለው፤ ስለዚህ ዕልፍ ብሎ ቆመ።
31ከዚያም ኢትዮጵያዊው ደርሶ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ የምሥራች! ዛሬ እግዚአብሔር ከተነሡብህ ጠላቶችህ ሁሉ ታድጎሃል” አለው።
32ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን፣ “ብላቴናው አቤሴሎም ደኅና ነውን?” ሲል ጠየቀው።
ኢትዮጵያዊውም፣ “የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶችና ሊጐዱህ የሚነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ወጣት ይሁኑ” ሲል መለሰ።
33ንጉሡም እጅግ ዐዘነ፤ በቅጽር በሩ ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” ይል ነበር።
Currently Selected:
2 ሳሙኤል 18: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.