የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ነገሥት 7:1-12

2 ነገሥት 7:1-12 NASV

ኤልሳዕም፣ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በነገው ዕለት በዚሁ ሰዓት፣ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ ማለፊያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ይሸጣል’ ” አለ። ንጉሡ በክንዱ ላይ የተደገፈውም የጦር አለቃ፣ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እንዲያው ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር የሰማያትን መስኮቶች ቢከፍት እንኳ ይህ ሊሆን ይችላልን?” ሲል ጠየቀው። ኤልሳዕም፣ “ይህን አንተው ራስህ በዐይንህ ታየዋለህ፤ ይሁን እንጂ ከዚያ አንዳች አትቀምስም” አለው። በዚህ ጊዜ የሚያሠቅቅ የቈዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች በከተማዪቱ መግቢያ በር አጠገብ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ በዚህ የምንቈየው ለምንድን ነው? ታዲያ፣ ‘ወደ ከተማዪቱ እንግባ ብንል’ በዚያም ራብ ስላለ እንሞታለን፤ በዚሁም ብንሆን ያው መሞታችን አይቀርም፤ ስለዚህ ወደ ሶርያውያኑ ሰፈር ዝም ብለን እንሂድ፤ ዝም ካሉን ሕይወታችን ትተርፋለች፤ ከገደሉንም ሞቶ መገላገል ነው።” ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ወደ ሰፈሩ ጥግ ሲደርሱም አንድም ሰው በዚያ አልነበረም። ይህ የሆነበትም ምክንያት፣ እግዚአብሔር የሠረገሎችንና የፈረሶችን እንዲሁም የብዙ ሰራዊት ድምፅ ሶርያውያን እንዲሰሙ አድርጎ ስለ ነበር ነው፤ እርስ በእርሳቸውም፣ “እነሆ፣ የእስራኤል ንጉሥ በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል፣ የኬጢያውያንንና የግብፃውያንን ነገሥታት ቀጥሮ አምጥቶብናል” ተባባሉ። ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውንም አልወሰዱም ነፍሳቸውን ብቻ ለማዳን ሲሉ ሰፈሩን እንዲሁ እንዳለ ትተው ሄዱ። ለምጽ ያለባቸውም ሰዎች ወደ ሰፈሩ አጠገብ ከደረሱ በኋላ፣ ከድንኳኖቹ ወደ አንዱ ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ተመልሰው በመምጣትም ወደ ሌላው ድንኳን ገብተው ሌሎች ነገሮችን በመውሰድ እንደዚሁ ደበቁ። እርስ በርሳቸውም፣ “ያደረግነው ትክክል አይደለም፤ ዕለቱ የምሥራች ቀን ነው፤ እኛ ግን የራሳችን ብቻ አደረግነው፤ እስኪነጋም ከቈየን በደለኞች እንሆናለን፤ ስለዚህ ወደ ቤተ መንግሥት በፍጥነት ሄደን እንንገር” ተባባሉ። ስለዚህ ሄደው የከተማዪቱን መግቢያ በር ጠባቂዎች ጮኸው በመጥራት፣ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገባን፤ እዚያም ከታሰሩ ፈረሶችና አህዮች በቀር አንድም ሰው አልነበረም፤ የማንም ድምፅ አልተሰማም፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ናቸው” ብለው ነገሯቸው። የበሩ ጠባቂዎችም ይህንኑ አስተጋቡ፤ ዜናውም በቤተ መንግሥቱ ተሰማ። ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለጦር አለቆቹ እንዲህ አላቸው፤ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ መራባችንን ስለሚያውቁ፣ ‘መቼም መውጣታቸው አይቀርም፤ ከዚያም ከነሕይወታቸው እንማርካቸዋለን፤ እኛም ሰተት ብለን ወደ ከተማዪቱ እንገባለን’ በማለት በገጠር ለመደበቅ ከሰፈራቸው ወጥተዋል።”