በዚህ ጊዜ ንዕማን የሶርያ ንጉሥ ጦር አዛዥ ነበረ፤ እግዚአብሔር በዚህ ሰው አማካይነት፣ ሶርያ ድልን እንድትጐናጸፍ ስላደረጋት በጌታው ዘንድ ታላቅና የተከበረ ሰው ነበር። ጀግና ወታደር ቢሆንም ለምጽ ወጥቶበት ነበር። አደጋ ጣዮች ከሶርያ ወጥተው፣ ከእስራኤል ምድር አንዲት ልጃገረድ ማረኩ፤ እርሷም የንዕማንን ሚስት ታገለግላት ነበር። እመቤቷንም፣ “ጌታዬ በሰማርያ ያለውን ነቢይ ሄዶ ቢያገኘው እኮ ከዚህ ለምጹ ይፈውሰው ነበር” አለቻት። ንዕማንም ወደ ጌታው ሄዶ ከእስራኤል የመጣችው ልጃገረድ ያለችውን ነገረው። የሶርያም ንጉሥ፣ “በል እንግዲያው አሁኑኑ ሂድ፤ እኔም ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እጽፋለሁ” አለው፤ ስለዚህ ንዕማን ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺሕ ሰቅል ወርቅና ዐሥር ሙሉ ልብስ ይዞ ሄደ። ለእስራኤልም ንጉሥ የያዘው ደብዳቤ፣ “ከለምጹ እንድትፈውሰው ይህን ደብዳቤ አስይዤ አገልጋዬን ንዕማንን ወደ አንተ ልኬዋለሁ” የሚል ነው። የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ወዲያው እንዳነበበ ልብሱን ቀድዶ፣ “ከለምጽ እንድፈውሰው ይህን ሰው ወደ እኔ መላኩ እኔ ገድዬ ማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? እንግዲህ ጠብ ሲፈልገኝ እዩ!” አለ። የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ፣ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን መቅደዱን በሰማ ጊዜ፣ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “ልብስህን ለምን ቀደድህ? ሰውየው ወደ እኔ ይምጣ፤ ከዚያም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን ያውቃል።” ስለዚህ ንዕማን በፈረሶቹና በሠረገሎቹ ሆኖ በኤልሳዕ ቤት ደጃፍ ሲደርስ ቆመ። ኤልሳዕም፣ “ሂድና በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህ ይፈወሳል፤ አንተም ትነጻለህ” ብሎ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከበት። ንዕማን ግን ተቈጥቶ እንዲህ በማለት ሄደ፤ “እኔ እኮ በርግጥ ወደ እኔ መጥቶ በመቆም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፣ በእጁም ዳስሶ ከለምጽ በሽታዬ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር። ለዚህ ለዚህ የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋር ከየትኞቹም የእስራኤል ውሆች አይሻሉምን? ለመታጠብ ለመታጠብማ በእነርሱ ታጥቤ መንጻት አልችልምን?” ስለዚህ በቍጣ ተመለሰ። የንዕማን አገልጋዮች ግን ወደ እርሱ ቀርበው፣ “አባት ሆይ፤ ነቢዩ ከዚህ ከበድ ያለ ነገር እንድታደርግ ቢነግርህ ኖሮ አታደርገውም ነበርን? ታዲያ፣ ‘ታጠብና ንጻ’ ቢልህ ምኑ አስቸገረህ?” አሉት። ስለዚህ ንዕማን ወረደ፤ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገረውም በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ትንሽ ልጅ ሥጋ ሆነ፤ ነጻም።
2 ነገሥት 5 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ነገሥት 5
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ነገሥት 5:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos