2 ነገሥት 22
22
የሕጉ መጽሐፍ ተገኘ
22፥1-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 34፥1-2፤ 34፥8-28
1ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም የቦጽቃት አገር ሰው የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች። 2እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ።
3በዘመነ መንግሥቱ በዐሥራ ስምንተኛውም ዓመት ኢዮስያስ የሜሶላምን የልጅ ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ጸሓፊውን ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላከው፤ እንዲህም አለው፤ 4“ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ ውጣ፤ የበር ጠባቂዎች ከሕዝቡ ሰብስበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባው ገንዘብ ምን ያህል እንደ ሆነ ራሱ እንዲቈጥረው አድርግ፤ 5ይህም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚያድሱት ይክፈሏቸው፤ 6የሚከፍሉትም ለየእጅ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ ዕድሳት ሥራ የሚሆኑ ዕንጨቶችና ጥርብ ድንጋዮች ይግዙበት። 7ሰዎቹ ታማኞች ስለ ሆኑም የተሰጣቸውን ገንዘብ መቈጣጠር አያስፈልግም።”
8ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ እኮ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” ብሎ ሰጠው፤ እርሱም ተቀብሎ አነበበው። 9ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ሄዶ ንጉሡን እንዲህ አለው፣ “ሹማምትህ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተው ቤተ መቅደሱን እየተቈጣጠሩ ለሚያሠሩት አስረክበዋል።” 10ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ለንጉሡ፣ “ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” ብሎ ነገረው። ሳፋንም ለንጉሡ ከመጽሐፉ አነበበለት።
11ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ። 12ከዚያም ንጉሡ ካህኑን ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓክቦርን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ 13“ሂዱና ስለ እኔ፣ ስለ ሕዝቡና ስለ ይሁዳም ሁሉ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ለዚህ መጽሐፍ ቃል ባለመታዘዛቸው፣ እኛን በተመለከተም በዚሁ ላይ የተጻፈውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፣ በእኛ ላይ የነደደው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና።”
14ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦርና፣ ሳፋን፣ ዓሳያም የሐርሐስ የልጅ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የአልባሳት ጠባቂውን የሴሌምን ሚስት ነቢዪቱን ሕልዳናን ለመጠየቅ ሄዱ። እርሷም ምክር በጠየቋት ቦታ፣ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው የከተማው ክፍል ትኖር ነበር።
15ነቢዪቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ 16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ የተጻፈውን ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ስፍራና በነዋሪዎቹ ላይ አመጣለሁ። 17እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና በእጆቻቸው ሥራ ሁሉ#22፥17 ወይም ባደረጉት ነገር ሁሉ ለቍጣ ስላነሣሡኝ፣ ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።’ 18እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ 19ለርግማንና#22፥19 ማለትም ስማቸው ለርግማን ይሆናል (ኤር 29፥22)፤ ወይም ሌሎች እነርሱ የተረገሙ እንደ ሆኑ ያያሉ። ለጥፋት የተዳረጉ ስለ መሆናቸው በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገርኩትን በሰማህ ጊዜ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔር ፊት ራስህን ስላዋረድህ፣ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ ስላለቀስህ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር። 20ስለዚህ፣ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ”
ሰዎቹም መልሷን ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 22: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.