2 ነገሥት 21
21
የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ
21፥1-10 ተጓ ምብ – 2ዜና 33፥1-10
21፥17-18 ተጓ ምብ – 2ዜና 33፥18-20
1ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐምሳ ዐምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሐፍሴባ ትባል ነበር። 2እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያስወጣቸውን የአሕዛብን አስጸያፊ ልማድ በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 3አባቱ ሕዝቅያስ የደመሰሳቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም ለበኣል መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ምስል ዐምዶች ሠራ። እንዲሁም ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም። 4እግዚአብሔር፣ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያዎችን ሠራ። 5በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ። 6የገዛ ወንድ ልጁን በእሳት ሠዋ#21፥6 ወይም፣ የራሱን ልጅ በዚህ ውስጥ እንዲያልፍ አደረገ።፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቍጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
7ያበጀውን የአሼራን የተቀረጸ ምስል ወስዶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስቀመጠ፤ ይህም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ” ያለው ስፍራ ነው። 8እንዲሁም፣ “ብቻ ያዘዝኋቸውን ሁሉ ተጠንቅቀው በመፈጸምና ባሪያዬ ሙሴ የሰጣቸውንም ሕግ በሙሉ በመጠበቅ ይጽኑ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር፣ ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም” ያለው ስለዚሁ ስፍራ ነው። 9ሕዝቡ ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምናሴ አሳታቸው።
10 እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፤ 11“የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አስጸያፊ ኀጢአት ሠርቷል፤ ከርሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን ይልቅ ክፉ ድርጊት ፈጽሟል፤ ይሁዳንም በጣዖታቱ አስቷል። 12ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ለሚሰማ ሁሉ ጆሮዎቹ ጭው እንዲሉ የሚያደርግ ክፉ መከራ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። 13በሰማርያ ላይ ያዘጋጀሁትን መለኪያ ገመድ፣ የአክዓብንም ቤት የለካሁበትን ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ አንድ ሰው ሳሕን እንደሚወለውል ከወለወለም በኋላ እንደሚገለብጠው እኔም ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ። 14የርስቴንም ቅሬታ እተዋቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ብዝበዛና ምርኮ ይሆናሉ። 15ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለ ፈጸሙና ለቍጣ ስላነሣሡኝ ነው።’ ”
16ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።
17በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ የሠራውን ኀጢአት ጨምሮ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 18ምናሴም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ “የዖዛ አትክልት” በሚባለው በቤተ መንግሥቱ አትክልት ውስጥ ተቀበረ። ልጁ አሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አሞን
21፥19-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 33፥21-25
19አሞን በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ሜሶላም ትባላለች፤ እርሷም የዮጥባ አገር ሰው የሐሩስ ልጅ ነበረች። 20አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 21አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱ ያመለካቸውን አማልክት አመለከ፤ ሰገደላቸውም። 22የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፤ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።
23የአሞንም ሹማምት በርሱ ላይ አሢረው፤ ንጉሡንም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት። 24ከዚያም የአገሩ ሕዝብ በንጉሥ አሞን ላይ ያሤሩትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በምትኩ አነገሡት።
25በአሞን ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 26እርሱም በዖዛ አትክልት ውስጥ ባለው መቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
Currently Selected:
2 ነገሥት 21: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.