የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ነገሥት 11

11
ጎቶልያና ኢዮአስ
11፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥10–23፥21
1የአካዝያስ እናት ጎቶልያ ልጇ መሞቱን በሰማች ጊዜ፣ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብ በሙሉ አጠፋች። 2የንጉሥ ኢዮራም ልጅ፣ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት ግን የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሊገደሉ ከነበሩት ልዑላን መካከል ሰርቃ ወሰደችው። እንዳይገድሉትም ከጎቶልያ በመደበቅ እርሱንና ሞግዚቱን በአንድ እልፍኝ ሸሸገቻቸው። 3ጎቶልያ አገሩን በምትገዛበት ጊዜም ከሞግዚቱ ጋር ስድስት ዓመት በእግዚአብሔር ቤት ተሸሸገ።
4በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ ካራውያንንና ዘብ ጠባቂዎቹን የሚያዝዙትን የመቶ አለቆች እርሱ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አደረገ። ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን በማድረግ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስማላቸው፤ ከዚያም የንጉሡን ልጅ አሳያቸው። 5እንዲህም ሲል አዘዛቸው፤ “እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሦስት ምድብ ሆናችሁ በሰንበት ዕለት ዘብ ከምትጠብቁት መካከል አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤ 6ሌላው ከሦስት አንዱ የሱርን በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሌላው አንድ ሦስተኛው እጅ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ተራ ገብቶ ከሚጠብቀው ከዘብ ጥበቃው ኋላ ያለውን በር ይጠብቅ። 7እናንተ እንደ ተለመደው በሰንበት ዕለት ከዘብ ጥበቃ ነጻ የምትሆኑት ሁለት ሦስተኛው እጅ ግን ንጉሡ ያለበትን ቤተ መቅደስ ጠብቁ። 8ሁላችሁም መሣሪያችሁን ይዛችሁ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ የሚቀርባችሁ ቢኖር#11፥8 ወይም፣ ወደ ቅጥራችሁ የሚደርስ ቢኖር ግን ይገደል። ንጉሡ በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ አትለዩት።”
9የመቶ አለቆቹም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም በሰንበት ዕለት ለዘብ ጥበቃ የሚገቡትንና ከዘብ ጥበቃ የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ። 10ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሥ ዳዊትን ጦርና ጋሻ ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። 11ወታደሮቹም እያንዳንዳቸው መሣሪያቸውን ይዘው፣ ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ።
12ዮዳሄም የንጉሡን ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነለት፤ የኪዳኑንም መጽሐፍ ሰጠው፣ መንገሡን ዐወጀ፤ ኢዮአስም ተቀብቶ ነገሠ። ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ሺሕ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።
13ጎቶልያም የሰራዊቱንና የሕዝቡን ጩኸት በሰማች ጊዜ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ ቤተ መቅደሱ ሄደች። 14እነሆ፤ በወጉ መሠረት ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ ሹማምቱና መለከት ነፊዎቹ ከአጠገቡ ሆነው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር። ጎቶልያም ልብሷን ቀድዳ፣ “ይህ ክሕደት ነው! ክሕደት ነው!” በማለት ጮኸች።
15ካህኑ ዮዳሄም ጭፍሮቹን የሚያዝዙትን የመቶ አለቆች፣ “በረድፍ በተሰለፉት ጭፍሮች መካከል አውጧት፤#11፥15 ወይም፣ ከቅጥራችሁ መካከል የሚከተላትንም ሁሉ በሰይፍ በሉት” ሲል አዘዘ፤ ይህ የሆነውም ካህኑ አስቀድሞ፣ “በእግዚአብሔር ቤት መገደል የለባትም” በማለቱ ነበር። 16ስለዚህ ፈረሶች ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚገቡበት ስፍራ ስትደርስ፣ ይዘው እዚያው ገደሏት።
17ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን እንዲኖር አደረገ፤ እንደዚሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን መሠረተ። 18የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ሄደው አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሁሉ ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።
ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ። 19ከዚያም መቶ አለቆቹን፣ ካራውያንንና ዘበኞቹን እንዲሁም የአገሩን ሕዝብ በሙሉ በመያዝ ሁሉም በአንድነት ሆነው፣ ንጉሡን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወስደው በዘብ ጠባቂዎች ቅጥር በር በኩል ታች ወዳለው ቤተ መንግሥት ይዘውት ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ 20የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አለው፤ ጎቶልያ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሰይፍ ተገድላ ስለ ነበር፣ ከተማዪቱ ጸጥ አለች። 21ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።

Currently Selected:

2 ነገሥት 11: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ