የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ነገሥት 1:7-17

2 ነገሥት 1:7-17 NASV

ንጉሡም፣ “ለመሆኑ ሊገናኛችሁ መጥቶ እንዲህ ያላችሁ ሰው እንዴት ያለ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰውየው ጠጕራም፣ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር” አሉት። ንጉሡም፣ “ዐወቅሁት፤ ቴስብያዊው ኤልያስ ነው” አላቸው። ከዚያም ንጉሡ አንድ የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ወታደሮቹ ጋራ ወደ ኤልያስ ላከ። የዐምሳ አለቃውም ኤልያስ ወደ ተቀመጠበት ኰረብታ ጫፍ ወጥቶ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘ና ውረድ’ ይልሃል” አለው። ኤልያስም መልሶ የዐምሳ አለቃውን፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ፣ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ አንተንና ዐምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው። ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ የዐምሳ አለቃውንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች። እንደ ገናም ንጉሡ ሌላ የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ሰዎቹ ጋራ ላከ፤ የዐምሳ አለቃውም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘አሁኑኑ ና ውረድ’ ይልሃል” አለው። ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ እሳት ከሰማይ ወርዳ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው፤ ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች። ስለዚህም ንጉሡ ሦስተኛውን የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ሰዎቹ ጋራ ላከ። ይህም ሦስተኛው የዐምሳ አለቃ ወጥቶ፣ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ እባክህ የእኔና የእነዚህ የዐምሳዎቹ አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን። እነሆ፤ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ የፊተኞቹን ሁለት ዐምሳ አለቆችና ሰዎቻቸውን ሁሉ በላች፤ አሁን ግን ሕይወቴ በፊትህ የከበረች ትሁን።” የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን፣ “ዐብረኸው ውረድ፤ ደግሞም አትፍራው” አለው። ስለዚህ ኤልያስ ተነሣ፤ ዐብሮትም ወደ ንጉሡ ወረደ። ንጉሡንም፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለመሆኑ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ስለ ራስህ ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክኸው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን? ይህን በማድረግህም ከተኛህበት ዐልጋ ፈጽሞ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ’ ” ብሎ ነገረው። ስለዚህ አካዝያስ ኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ። አካዝያስ ወንድ ልጅ ስላልነበረው፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}