የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ዜና መዋዕል 9

9
የሳባ ንግሥት ሰሎሞንን ጐበኘች
9፥1-12 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥1-13
1የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ቅመማ ቅመም፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን በግመሎች አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋራ ደረሰች፤ ወደ ሰሎሞንም ቀርባ በልቧ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ከሰሎሞን የተሰወረና ሊመልስላት ያልቻለው አንድም ጥያቄ አልነበረም 3የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፣ የሠራውን ቤተ መንግሥት፣ 4እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ የአስተናባሪዎቹን አቋቋምና የደንብ ልብሳቸውን፣ ጠጅ አሳላፊዎቹንና አለባበሳቸውን እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች#9፥4 ወይም ወደ ላይ የሚወጣባቸውን ደረጃዎች ተብሎ መተርጐም ይቻላል። ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች።
5ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስለ ተናገርሃቸው ነገሮችና#9፥5 ወይም ስላከናወንሃቸው ነገሮች ወይም ስላገኘሃቸው ስኬቶች ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት እውነት ነው። 6ይሁን እንጂ መጥቼ የነገሩኝን በዐይኔ እስካይ ድረስ አላመንሁም ነበር፤ በርግጥም የጥበብህ ታላቅነት እኩሌታው እንኳ አልተነገረኝም፤ እኔ ከሰማሁት ዝና እጅግ ይልቃል። 7ሰዎችህ እንዴት ብፁዓን ናቸው! ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ ምንኛ ብፁዓን ናቸው! 8በአንተ ደስ ተሰኝቶ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ንጉሥ ሆነህ እንድትገዛ፣ በዙፋኑ ላይ ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ አምላክህ ለእስራኤል ካለው ፍቅርና ለዘላለም ሊያጸናቸው ካለው ፍላጎት የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን ታደርግ ዘንድ አንተን በላያቸው ላይ አንግሦሃል።”
9ከዚያም ለንጉሡ አንድ መቶ ሃያ መክሊት#9፥9 4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመሞችና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን እንደ ሰጠችው ዐይነት ቅመማ ቅመም ያለ ከቶ አልነበረም።
10የኪራም ሰዎችና የሰሎሞን ሰዎች ከኦፊር ወርቅ እንደዚሁም ሰንደልና#9፥10 የአልሙግ ዕንጨት ሊሆን ይችላል። የከበሩ ድንጋዮች አመጡ። 11ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ ደረጃ መሥሪያ እንደዚሁም ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው፤ ይህን የመሰለ ነገር በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም።
12ንጉሥ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ስጦታውም እርሷ ካመጣችለት በላይ ነበር። ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋራ ወደ አገሯ ተመለሰች።
የሰሎሞን ብልጽግና
9፥13-28 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥14-292ዜና 1፥14-17
13ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት#9፥13 23 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። የሚመዝን ወርቅ ነበር። 14ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር። መላው የዐረብ ነገሥታትና አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር።
15ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ ትላልቅ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ስድስት መቶ ሰቅል ጥፍጥፍ ወርቅ#9፥15 6.9 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ነበር። 16እንዲሁም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእነዚህም በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል#9፥16 3.5 ኪሎ ግራም ይህል ነው ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖረ።
17ከዚያም ንጉሡ በዝኆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው። 18ዙፋኑ ባለስድስት ደረጃ ሲሆን፣ ከዙፋኑ ጋራ የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሲሆን፣ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። 19በስድስቱም ደረጃዎች ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ተሠርቶ አያውቅም። 20ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም። 21ንጉሡ በኪራም ሰዎች የሚነዱ የተርሴስ#9፥21 ሰብዓ ሊቃናት፣ የንግድ መርከቦች ይላል። መርከቦች ነበሩት፤ እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እየያዙ ይመለሱ ነበር።
22ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር። 23የምድር ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋራ መገናኘት ይፈልጉ ነበር። 24በየዓመቱም የሚመጣው ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ቅመማ ቅመም፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር።
25ሰሎሞን አራት ሺሕ የፈረሶችና የሠረገሎች#9፥25 ወይም፣ ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ጋጥ ነበረው፤ እንዲሁም ንጉሡ በሚኖርበት በኢየሩሳሌምና በሠረገላ ከተሞች ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት። 26እርሱም ከኤፍራጥስ ወንዝ#9፥26 የኤፍራጥስ ወንዝ ነው፤ ነገር ግን አንዳንድ ቅጆች ኤፍራጥስ የሚለውን ቃል አይጨምሩም እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ። 27ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 28የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብጽና ከሌሎች አገሮች ነበር።
የሰሎሞን መሞት
9፥29-31 ተጓ ምብ – 1ነገ 11፥41-43
29የቀረው፣ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ሥራ፣ ጥበቡም በነቢዩ በናታን ታሪክና በሴሎናዊው በአኪያ ትንቢት እንዲሁም ባለራእዩ አዶ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው ራእይ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 30ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ተቀምጦ በመላው እስራኤል ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31ከዚያም ሰሎሞን ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማ ቀበሩት። ልጁም ሮብዓም በርሱ ፈንታ ነገሠ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ