2 ዜና መዋዕል 9
9
የሳባ ንግሥት ሰሎሞንን ጐበኘች
9፥1-12 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥1-13
1የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ቅመማ ቅመም፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን በግመሎች አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ደረሰች፤ ወደ ሰሎሞንም ቀርባ በልቧ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ሊመልስላት የተሳነው አንዳች ነገር አልነበረም። 3የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብና የሠራውን ቤተ መንግሥት፣ 4በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አስተናባሪዎቹንና አለባበሳቸውን፣ ጠጅ አሳላፊዎቹንና አለባበሳቸውን እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች#9፥4 ወይም ወደ ላይ የሚመጣባቸውን ደረጃዎች ተብሎ መተርጐም ይቻላል። ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች። 5ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስለ ሥራህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው። 6ነገር ግን መጥቼ በዐይኔ እስካየሁ ጊዜ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ በርግጥም የጥበብህ እኩሌታ እንኳ አልተነገረኝም፤ እኔ ከሰማሁት ዝና እጅግ ትልቃለህ። 7ሰዎችህ ምንኛ ታድለዋል! ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ ምንኛ ታድለዋል! 8ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ንጉሥ ሆነህ እንድትገዛ፣ በአንተ ደስ የተሰኘውና በዙፋኑ ላይ ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ አምላክህ ለእስራኤል ካለው ፍቅርና ለዘላለም ሊያጸናቸው ካለው ፍላጎት የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን ታደርግ ዘንድ አንተን በላያቸው ላይ አንግሦሃልና።”
9ከዚያም ለንጉሡ አንድ መቶ ሃያ መክሊት#9፥9 4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ቅመማ ቅመምና የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰሎሞን እንደ ሰጠችው ዐይነት ቅመማ ቅመም ያለ ከቶ አልነበረም።
10የኪራም ሰዎችና የሰሎሞን ሰዎች ወርቅ ከኦፊር እንደዚሁም ሰንደልና#9፥10 የአልሙግ ዕንጨት ሊሆን ይችላል የከበሩ ድንጋዮች አመጡ። 11ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ ደረጃ መሥሪያ እንደዚሁም ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው፤ ይህን የመሰለ ነገር በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም።
12ንጉሥ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ስጦታውም እርሷ ካመጣችለት በላይ ነበር። ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ አገሯ ተመለሰች።
የሰሎሞን ብልጽግና
9፥13-28 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥14-29፤ 2ዜና 1፥14-17
13ሰሎሞን በየዓመቱ የሚቀበለው ወርቅ ክብደቱ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት#9፥13 23 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ነበር። 14ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር፤ እንዲሁም መላው የዐረብ ነገሥታትና የገዛ ምድሩ አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር።
15ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ የተሠራ ታላላቅ ጋሻዎች አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል#9፥15 3.5 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ነበር። 16እንዲሁም ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎች በጥፍጥፍ ወርቅ ሠራ፤ በእነዚህም በእያንዳንዳቸው የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል#9፥16 1.7 ኪሎ ግራም ይህል ነው ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖራቸው።
17ከዚያም ንጉሡ በዝኆን ጥርስ ያጌጠና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ትልቅ ዙፋን ሠራ። 18ዙፋኑ ስድስት መውጫ መውረጃ ደረጃዎች ሲኖሩት፣ ከዙፋኑ ጋር የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሆኖም ከመደገፊያዎቹም አጠገብ አንዳንድ አንበሳ ቆሞ ነበር። 19እንዲሁም በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር ላይ አንዳንድ አንበሳ፣ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር ተሠርቶ አያውቅም። 20ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደንቃ” ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም። 21ንጉሡ በኪራም ሰዎች የሚነዱ የንግድ መርከቦች ነበሩት፤#9፥21 ዕብራይስጡ፣ ወደ ተርሴስ ሊሄዱ የሚችሉ መርከቦች ይላል። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እየያዙ ይመለሱ ነበር።
22ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የበለጠ ነበር። 23የምድር ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋር መገናኘት ይፈልጉ ነበር። 24በየዓመቱ ወደ እርሱ የሚመጡትም ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ የልብስ፣ የጦር መሣሪያና የቅመማ ቅመም እንደዚሁም የፈረስና የበቅሎ ገጸ በረከት ያመጡለት ነበር።
25ሰሎሞን አራት ሺሕ የፈረሶችና የሠረገሎች#9፥25 ወይም፣ ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ጋጥ ነበረው፤ እንዲሁም በሚኖርበት በኢየሩሳሌምና በሰረገላ ከተሞች ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት። 26እርሱም ከኤፍራጥስ ወንዝ#9፥26 የኤፍራጥስ ወንዝ ነው፤ ነገር ግን አንዳንድ ቅጆች ኤፍራጥስ የሚለውን ቃል አይጨምሩም እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ዳርቻ ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ። 27ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 28ለሰሎሞን ከግብፅና#9፥28 በኪልቂያ የምትገኘው ሙዙር ነች። ከሌሎች አገሮች ሁሉ ፈረሶች ያመጡለት ነበር።
የሰሎሞን መሞት
9፥29-31 ተጓ ምብ – 1ነገ 11፥41-43
29ሰሎሞን በዘመነ መንግሥቱ የሠራው ሌላው ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክና በሴሎናዊው በአሒያ ትንቢት እንዲሁም ባለ ራእዩ አዶ ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው ራእይ ውስጥ የተጻፈ አይደለምን? 30ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ተቀምጦ በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31ከዚያም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 9: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.