2 ዜና መዋዕል 7
7
የቤተ መቅደሱ መመረቅ
7፥1-10 ተጓ ምብ – 1ነገ 8፥62-66
1ሰሎሞን ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ፣ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው። 2የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ስለ ሞላው ካህናቱ ወደዚያ መግባት አልቻሉም። 3እስራኤላውያንም ሁሉ እሳቱ ሲወርድ፣ የእግዚአብሔርንም ክብር ከቤተ መቅደሱ በላይ ሲያዩ፣ በመተላለፊያው ወለል ላይ ተንበረከኩ፤ በግንባራቸውም ወደ መሬት ተደፍተው ሰገዱ፤ እንዲህ እያሉም ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ፤
“እርሱ ቸር ነውና፤
ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”
እያሉም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
4ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ። 5ንጉሥ ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺሕ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺሕ በግና ፍየል ሠዋ፤ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በዚህ ሁኔታ ቀደሱ። 6ካህናቱም እንደ ሌዋውያኑ፣ ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር እንዲወደስበት የሠራውንና “ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት እግዚአብሔርን ባመሰገነ ጊዜ፣ የተቀመጠበትን የእግዚአብሔርን የዜማ መሣሪያ ይዘው በተመደበላቸው ስፍራ ቆሙ። ካህናቱ በሌዋውያኑ ትይዩ ሆነው መለከቶቻቸውን ሲነፉም እስራኤላውያን ሁሉ ቆመው ነበር።
7ሰሎሞን የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን ቍርባንና ሥቡን መያዝ ስላልቻለ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የመካከለኛውን አደባባይ ክፍል ቀድሰው፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን#7፥7 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። ስብ በዚያ አቃጠለ።
8በዚያ ጊዜም ሰሎሞን ዐብረውት ከነበሩት ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋራ ለሰባት ቀን በዓሉን አከበረ፤ ሕዝቡም ከሐማት መግቢያ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ካለው ምድር የመጣ እጅግ ታላቅ ጉባኤ ነበር። 9መሠዊያውን ለሰባት ቀን ስለ ቀደሱና የሰባት ቀን በዓል በተጨማሪ ስላከበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ። 10ሰሎሞንም በሰባተኛው ወር፣ በሃያ ሦስተኛው ቀን ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን እንዲሁም ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው በጎ ነገር ሁሉ ከልብ ተደስተው ሐሤት እያደረጉ ወደ የቤታቸው ተመለሱ።
እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገለጠለት
7፥11-22 ተጓ ምብ – 1ነገ 9፥1-9
11ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና ቤተ መንግሥቱን ሠርቶ ከጨረሰና፤ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ያደርግ ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ 12እግዚአብሔር ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦለት እንዲህ አለው፤
“ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንም ስፍራ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤተ መቅደስ እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ።
13“ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን በምዘጋበት ጊዜ ወይም ምድሪቱን እንዲበላ አንበጣ በማዝዝበት ጊዜ፣ ወይም በሕዝቤ ላይ ቸነፈር በምሰድድበት ጊዜ፣ 14በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ። 15አሁንም በዚህ ስፍራ ወደሚጸለየው ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ። 16ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ፤ ቀድሼዋለሁም። ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።
17“አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በፊቴ ብትሄድ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቶቼንና ሕጎቼን ብትጠብቅ፣ 18ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘እስራኤልን የሚገዛ ሰው ከዘርህ አታጣም’ በማለት በሰጠሁት ተስፋ መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።
19“እናንተ ግን እኔን ከመከተል ተመልሳችሁ የሰጠኋችሁን ሥርዐቶቼንና ትእዛዞቼን ብትተዉ፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብታመልኳቸው፣ 20በዚያ ጊዜ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድሬ እነቅላቸዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስ እተወዋለሁ፤ በሕዝቦችም ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ አደርገዋለሁ። 21ይህ ቤተ መቅደስ አሁን እጅግ የሚያስደንቅ ቢሆንም በዚያ የሚያልፍ ሁሉ ይገረማል፤ ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያደረገው ስለ ምን ይሆን?’ ይላል፤ 22ሰዎቹም መልሰው፣ ‘አዎን እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው አባቶቻቸውን ከግብጽ ምድር ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎች አማልክትን በመከተል ስላመለኳቸውና ስላገለገሏቸው ነው’ ይላሉ።”
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 7: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.