2 ዜና መዋዕል 7:1-10

2 ዜና መዋዕል 7:1-10 NASV

ሰሎሞን ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ፣ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን ሞላው። የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ስለ ሞላው ካህናቱ ወደዚያ መግባት አልቻሉም። እስራኤላውያንም ሁሉ እሳቱ ሲወርድ፣ የእግዚአብሔርንም ክብር ከቤተ መቅደሱ በላይ ሲያዩ፣ በመተላለፊያው ወለል ላይ ተንበረከኩ፤ በግንባራቸውም ወደ መሬት ተደፍተው ሰገዱ፤ እንዲህ እያሉም ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ፤ “እርሱ ቸር ነውና፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” እያሉም እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አቀረቡ። ንጉሥ ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺሕ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺሕ በግና ፍየል ሠዋ፤ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በዚህ ሁኔታ ቀደሱ። ካህናቱም እንደ ሌዋውያኑ፣ ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር እንዲወደስበት የሠራውንና “ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት እግዚአብሔርን ባመሰገነ ጊዜ፣ የተቀመጠበትን የእግዚአብሔርን የዜማ መሣሪያ ይዘው በተመደበላቸው ስፍራ ቆሙ። ካህናቱ በሌዋውያኑ ትይዩ ሆነው መለከቶቻቸውን ሲነፉም እስራኤላውያን ሁሉ ቆመው ነበር። ሰሎሞን የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን ቍርባንና ሥቡን መያዝ ስላልቻለ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የመካከለኛውን አደባባይ ክፍል ቀድሰው፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ በዚያ አቃጠለ። በዚያ ጊዜም ሰሎሞን ዐብረውት ከነበሩት ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋራ ለሰባት ቀን በዓሉን አከበረ፤ ሕዝቡም ከሐማት መግቢያ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ካለው ምድር የመጣ እጅግ ታላቅ ጉባኤ ነበር። መሠዊያውን ለሰባት ቀን ስለ ቀደሱና የሰባት ቀን በዓል በተጨማሪ ስላከበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ። ሰሎሞንም በሰባተኛው ወር፣ በሃያ ሦስተኛው ቀን ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን እንዲሁም ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው በጎ ነገር ሁሉ ከልብ ተደስተው ሐሤት እያደረጉ ወደ የቤታቸው ተመለሱ።