በዚህ ዐይነት የፋሲካን በዓል በማክበርና የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ በማቅረብ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በዚያ ቀን ተከናወነ። በዚያ ጊዜ በስፍራው የተገኙ እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ የቂጣንም በዓል እንደዚሁ ሰባት ቀን አከበሩ። ከነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንዲህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመላው ይሁዳና ከእስራኤል፣ በዚያ ከነበሩትም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋራ እንዳከበረው አድርጎ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም። ይህ ፋሲካ የተከበረው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ነበር። ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን አደራጅቶ ባጠናቀቀ ጊዜ፣ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ። ኒካዑ ግን መልእክተኛውን ልኮ፣ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተንና እኔን የሚያጣላን ምንድን ነው? ጦርነት ከገጠምሁት ቤት ጋራ እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንተን የምወጋህ አይደለሁም፤ እግዚአብሔር እንድፈጥን አዝዞኛል፤ ስለዚህ ከእኔ ጋራ ያለውን እግዚአብሔርን መቃወምህን ተው፤ አለዚያ ያጠፋሃል” አለው። ኢዮስያስ ግን ሌላ ሰው መስሎ በጦርነት ሊገጥመው ወጣ እንጂ ወደ ኋላ አልተመለሰም፤ በመጊዶ ሜዳ ላይ ሊዋጋው ሄደ እንጂ፣ ኒካዑ ከእግዚአብሔር ታዝዞ የነገረውን ሊሰማ አልፈለገም። ቀስተኞች ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ እርሱም የጦር መኰንኖቹን፣ “ክፉኛ ቈስያለሁና ከዚህ አውጡኝ” አላቸው። ስለዚህ ከሠረገላው አውርደው በራሱ ሠረገላ ላይ አስቀምጠውት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ እዚያም ሞተ፤ በአባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱለት። ኤርምያስ ለኢዮስያስ የሐዘን እንጕርጕሮ ግጥም ጻፈለት፤ ወንዶችና ሴቶች ሙሾ አውራጆች ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ግጥም ኢዮስያስን ያስታውሱታል፤ ይህም በእስራኤል የተለመደ ሆኖ በልቅሶ ግጥም መጽሐፍ ተጽፏል። በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ድርጊትና በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት ያከናወነው መንፈሳዊ ተግባር፣ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያደረገው ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።
2 ዜና መዋዕል 35 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ዜና መዋዕል 35
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ዜና መዋዕል 35:16-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች