2 ዜና መዋዕል 28
28
የይሁዳ ንጉሥ አካዝ
28፥1-27 ተጓ ምብ – 2ነገ 16፥1-20
1አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት ያደረገውን መልካም ነገር በእግዚአብሔር ፊት አላደረገም። 2እርሱም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ለበኣሊም ቀልጠው የተሠሩ ምስሎችን ሠራ። 3እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያስወገዳቸውን የአሕዛብን ርኩሰት ተከትሎ፣ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ዐጠነ፤ ወንዶች ልጆቹንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። 4በኰረብታ ላይ ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎችና በተራሮች ዐናት ላይ፣ በየዛፉም ጥላ ሥር መሥዋዕት አቀረበ፤ ዕጣንም ዐጠነ።
5ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር ለሶርያ ንጉሥ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም ድል አደረጉት፤ ከሕዝቡም ብዙዎቹን ምርኮኞች አድርገው ወደ ደማስቆ ወሰዷቸው። ደግሞም ለእስራኤል ንጉሥ ዐልፎ ተሰጠ፤ እርሱም ከባድ ጕዳት አደረሰበት። 6ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺሕ ወታደሮች ገደለ። 7ጦረኛው ኤፍሬማዊ ዝክሪም የንጉሡን ልጅ መዕሤያን፣ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን ዓዝሪቃምንና ለንጉሡ በማዕርግ ሁለተኛ ሰው የሆነውን ሕልቃናን ገደለ። 8እስራኤላውያንም ከገዛ ወገኖቻቸው ሁለት መቶ ሺሕ ባለትዳር ሴቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ማረኩ፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ ምርኮ ይዘው ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
9ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚያ ስለ ነበር፣ ሰራዊቱ ወደ ሰማርያ በተመለሰ ጊዜ ለመቀበል ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ እናንተ ግን እስከ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ፈጃችኋቸው። 10አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ወንዶችና ሴቶች፣ ባሪያዎቻችሁ ልታደርጓቸው ትፈልጋላችሁ፤ እናንተስ ብትሆኑ ኀጢአት ሠርታችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አልበደላችሁምን? 11እንግዲህ ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር አስፈሪ ቍጣ በእናንተ ላይ ነድዷልና፣ በምርኮ ያመጣችኋቸውን ወገኖቻችሁን መልሷቸው።”
12ከዚያም ከኤፍሬም መሪዎች ጥቂቶቹ የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፣ የምሺሌሞት ልጅ በራክያ፣ የሰሎም ልጅ ይሒዝቅያ፣ የሐድላይ ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን በመቃወም፣ 13“እነዚህን ምርኮኞች እዚህ ማምጣት አልነበረባችሁም፤ አለዚያ እኛ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች እንሆናለን፤ በኀጢአታችንና በበደላችን ላይ ሌላ ልትጨምሩ ታስባላችሁን? በደላችንማ ቀድሞውኑ በዝቷል፤ ቍጣውም በእስራኤል ላይ ነውና” አሉ።
14ስለዚህ ወታደሮቹ በሹማምቱና በጉባኤው ሁሉ ፊት ምርኮኞቹን ለቀቁ፤ የተማረከውንም ዕቃ መለሱ። 15በስም የተጠቀሱ ሰዎችም ምርኮኞቹን ተረክበው ዕራቍታቸውን ለቀሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሷቸው፤ ልብስና ጫማ፣ ምግብና መጠጥ ሰጧቸው፣ በቅባትም ቀቧቸው፤ የደከሙትንም ሁሉ በአህያ ላይ አስቀመጧቸው። ከዚያም ወገኖቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ከተማ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ኢያሪኮ ወስደዋቸው፣ ወደ ሰማርያ ተመለሱ።
16በዚያ ጊዜ ንጉሡ አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ልኮ ርዳታ ጠየቀ፤#28፥16 አንድ የዕብራይስጥ ቅጅ፣ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርስቱ ቅጅ እንዲሁም (2ነገ 16፥7) ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ትርጕሞች ግን ንጉሥ ይላሉ። 17ኤዶማውያን እንደ ገና መጥተው በይሁዳ ላይ አደጋ በመጣል ምርኮኞችን ወስደው ነበርና። 18ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በየኰረብታው ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ያሉትን ከተሞች በመውረር ቤትሳሚስን፣ ኤሎንን፣ ግዴሮትን፣ ሦኮን፣ ተምናን፣ ጊምዞንና በአካባቢያቸው የሚገኙትን መንደሮች ሁሉ ያዙ፤ ተቀመጡባቸውም። 19የእስራኤል#28፥19 በዜና መዋዕል ካልዕ መጽሐፍ ተደጋግሞ እንደ ተጠቀሰው ይህ ይሁዳ ነው። ንጉሥ አካዝ ክፋትን በይሁዳ ምድር ስላስፋፋና ለእግዚአብሔርም የነበረውን ታማኝነት በከፍተኛ ደረጃ ስላጓደለ፣ እግዚአብሔር ይሁዳን አዋረደ። 20የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ችግር ፈጠረበት እንጂ አልረዳውም። 21አካዝም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከቤተ መንግሥቱና ከመሳፍንቱ ዕቃዎች ዘርፎ ለአሦር ንጉሥ ሰጥቶት ነበር፤ ነገር ግን አልረዳውም።
22ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜም፣ ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነቱን ከምን ጊዜውም ይበልጥ አጓደለ፤ 23እርሱም “የሶርያ ነገሥታት አማልክት እነርሱን ስለ ረዷቸው፣ እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” ሲል እርሱን ላሸነፉት የደማስቆ አማልክት መሥዋዕት አቀረበ። ነገር ግን ለርሱና ለመላው እስራኤል መሰናክል ሆኑ።
24አካዝ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ ወሰደ#28፥24 ወይም ሰበረ ተብሎ መተርጐም ይችላል።፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየአውራ ጐዳናው ማእዘን ላይ መሠዊያ አቆመ። 25በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቃጥልባቸውን የኰረብታ መስገጃዎች ሠራ፤ በዚህም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ አነሣሣው።
26በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባርና አካሄዱ ሁሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል። 27አካዝ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በኢየሩሳሌምም ከተማ ተቀበረ፤ የተቀበረው ግን በእስራኤል ነገሥታት መካነ መቃብር አልነበረም። ልጁ ሕዝቅያስም በምትኩ ነገሠ።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 28: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.