2 ዜና መዋዕል 23:16-21

2 ዜና መዋዕል 23:16-21 NASV

ዮዳሄም ራሱ፣ ሕዝቡና ንጉሡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ሄደው የበኣልን ቤተ ጣዖት አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት። ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈውና ዳዊትም እንዳዘዘው፣ በደስታና በመዝሙር የሚቃጠለውን የእግዚአብሔርን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት ለመደባቸው ካህናትና ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ኀላፊነት ሰጣቸው። እንዲሁም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅጥር በሮች ላይ ጠባቆች አቆመ። የመቶ አለቆቹን፣ መኳንንቱን፣ የሕዝቡን ገዦችና የአገሩን ሕዝብ ሁሉ ይዞ ንጉሡን ከላይ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወደ ታች አመጣው። በላይኛውም መግቢያ በኩል ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብተው ንጉሡን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። መላውም የአገሩ ሕዝብ ተደሰተ፤ ጎቶልያ በሰይፍ ስለ ተገደለች ከተማዪቱ ጸጥ አለች።