2 ዜና መዋዕል 17
17
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ
1ልጁ ኢዮሣፍጥ በርሱ ፈንታ ነገሠ፤ በእስራኤል ላይ በረታ። 2እርሱም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ውስጥ ወታደር አኖረ፤ እንዲሁም በይሁዳ ምድርና አባቱ አሳ በያዛቸው በኤፍሬም መንደሮች ዘበኞች አስቀመጠ።
3በለጋነት ዕድሜው አባቱ ዳዊት በሄደበት መንገድ ስለ ሄደ፣ እግዚአብሔር ከኢዮሣፍጥ ጋራ ነበር፤ የበኣልንም አማልክት አልጠየቀም፤ 4ነገር ግን ከእስራኤል ድርጊት ይልቅ፣ የአባቱን ፈለገ፤ ትእዛዞቹንም ተከተለ። 5እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸናለት፤ መላው ይሁዳም ስጦታ ለኢዮሣፍጥ አመጣለት፤ ከዚህ የተነሣም ታላቅ ብልጽግናና ክብር አገኘ። 6ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ የጸና ነበር፤ እንደዚሁም ማምለኪያ ኰረብቶችንና የአሼራ ዐምዶችን ከይሁዳ አስወገደ።
7በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ ሹማምቱን፣ ማለትም ቤን ኀይልን፣ አብድያስን፣ ዘካርያስን፣ ናትናኤልንና ሚክያስን ላካቸው። 8ከእነዚህም ጋራ ጥቂት ሌዋውያን ነበሩ፤ ስማቸውም፦ ሸማያ፣ ነታንያ፣ ዝባድያ፣ አሣሄል፣ ሰሚራሞት፣ ዮናታን፣ አዶንያስ፣ ጦብያና ጦባዶንያ ነበር። ካህናቱ ደግሞ ኤሊሳማና ኢዮራም ነበሩ። 9እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በመሄድ በይሁዳ ሁሉ ላለው ሕዝብ አስተማሩ፤ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በመዘዋወርም ሕዝቡን አስተማሩ።
10በይሁዳ ዙሪያ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ስለ ወደቀባቸው ኢዮሣፍጥን አልተዋጉትም። 11ከፍልስጥኤማውያንም አንዳንዶቹ ለኢዮሣፍጥ እጅ መንሻ አመጡለት፤ ጥሬ ብርም ገበሩለት፤ ዐረቦችም ሰባት ሺሕ ሰባት መቶ አውራ በግና ሰባት ሺሕ ሰባት መቶ አውራ ፍየል መንጋ አመጡለት።
12ኢዮሣፍጥም እያየለ ሄደ፤ በይሁዳም ምሽጎችና የዕቃ ማከማቻ ከተሞች ሠራ። 13በይሁዳም ከተሞች እጅግ ብዙ ስንቅና ትጥቅ ነበረው። ደግሞም በቂ ልምድ ያላቸውን ተዋጊዎች በኢየሩሳሌም አስቀመጠ። 14እነርሱም በየቤተ ሰቦቻቸው ሲመዘገቡ እንደሚከተለው ነው፤
ከይሁዳ የየሻለቃው አዛዦች፣
አዛዡ ዓድና ከሦስት መቶ ሺሕ ተዋጊዎች ጋራ፤
15ከርሱ ቀጥሎም አዛዡ ይሆሐናን ከሁለት መቶ ሰማንያ ሺሕ ጋራ፤
16ከዚያ ቀጥሎም ለእግዚአብሔር አገልግሎት በፈቃደኛነት ራሱን የሰጠው የዝክሪ ልጅ ዓማስያ ከሁለት መቶ ሺሕ ተዋጊዎች ጋራ፤
17ከብንያምም ጀግናው ወታደር
ኤሊዳሄ ቀስትና ጋሻ ከያዙ ከሁለት መቶ ሺሕ ሰዎች ጋራ፤
18ቀጥሎም ዮዛባት ለጦርነት ዝግጁ ከሆኑ ከአንድ መቶ ሰማንያ ሺሕ ሰዎች ጋራ።
19እነዚህ እንግዲህ በመላው ይሁዳ በተመሸጉት ከተሞች ካስቀመጣቸው ሌላ፣ ንጉሡን ያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ናቸው።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 17: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.