2 ዜና መዋዕል 15
15
ንጉሥ አሳ ያደረገው ተሐድሶ
15፥16-19 ተጓ ምብ – 1ነገ 15፥13-16
1የእግዚአብሔር መንፈስ በዖዴድ ልጅ በአዛርያስ ላይ መጣ። 2እርሱም አሳን ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አሳ፣ እናንተም ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፤ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋራ ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋራ ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን፣ ይተዋችኋል። 3እስራኤል ያለ እውነተኛ አምላክ፣ ያለ አስተማሪ ካህንና ያለ ሕግ ብዙ ዘመን አሳልፈዋል። 4በመከራቸው ጊዜ ግን፣ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው። 5በዚያ ዘመን በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ ታላቅ ሁከት ስለ ነበር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት አስተማማኝ አልነበረም። 6እግዚአብሔር በተለያየ መከራ ያስጨንቃቸው ስለ ነበር፣ አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት፣ አንዱም ከተማ በሌላው ከተማ ይደመሰስ ነበር። 7እናንተ ግን የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ እጃችሁም አይላላ።”
8አሳ ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ልጅ#15፥8 የቩልጌትና የሱርስቱ ቅጅ (እንዲሁም ቍጥር 1) ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን የዖዴድን ልጅ የሚለውን አይጨምርም። የዓዛርያስን ትንቢት በሰማ ጊዜ በረታ። ከመላው ይሁዳና ከብንያም ምድር፣ በኤፍሬምም ኰረብቶች ላይ ከያዛቸው ከተሞች አስጸያፊዎቹን ጣዖታት አስወገደ። ከእግዚአብሔር መቅደስ ሰበሰብ ፊት ለፊት የነበረውንም የእግዚአብሔር መሠዊያ ዐደሰ።
9አምላኩ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ መሆኑን ባዩ ጊዜ፣ ከእስራኤል ብዙ ሰዎች እርሱን ተጠግተው ነበር፤ እርሱም ይሁዳንና ብንያምን እንዲሁም ከኤፍሬም፣ ከምናሴና ከስምዖን መጥተው ከእነርሱ ጋራ የተቀመጡትን ሰበሰበ።
10እነርሱም በአሳ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ዐምስተኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 11በዚያ ጊዜ በምርኮ ካመጡት ውስጥ ሰባት መቶ በሬ፣ ሰባት ሺሕ በግና ፍየል ለእግዚአብሔር ሠዉ። 12የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ። 13የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ ሁሉ ግን፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንድም ሆነ ሴት እንዲገደል አደረጉ። 14ይህንም በታላቅ ድምፅ፣ በእልልታ፣ በእንቢልታና በመለከት ድምፅ ለእግዚአብሔር ማሉ። 15በፍጹም ልባቸው ስለ ማሉም የይሁዳ ሕዝብ በመሐላው ደስ ተሠኙ። እግዚአብሔርን ከልብ ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጣቸው።
16እንዲሁም ንጉሡ አሳ ለአስጸያፊዋ የአሼራ ጣዖት ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው። 17አሳ የማምለኪያ ኰረብቶችን ከእስራኤል ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ፣ በዘመኑ ሁሉ ልቡ ፍጹም ነበር። 18እርሱና አባቱ የቀደሱትን ብር፣ ወርቅና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስገባ።
19እስከ ሠላሳ ዐምስተኛው የአሳ ዘመነ መንግሥት ድረስ ምንም ዐይነት ጦርነት አልነበረም።
Currently Selected:
2 ዜና መዋዕል 15: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.