የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ዜና መዋዕል 10

10
እስራኤል በሮብዓም ላይ ዐመፀ
10፥1–11፥4 ተጓ ምብ – 1ነገ 12፥1-24
1እስራኤላውያን ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ስለ ነበር፣ ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ሲሰማ፣ ከግብጽ ተመልሶ መጣ። 3ኢዮርብዓምንም ልከው አስጠሩት፤ ከዚያም እርሱና እስራኤል ሁሉ ወደ ሮብዓም ሄደው እንዲህ አሉት፤ 4“አባትህ ቀንበራችንን አከበደብን፤ አንተ ግን አስጨናቂውን ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር አቅልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን።”
5ሮብዓምም፣ “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ።
6ከዚያም ንጉሡ ሮብዓም አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ ካገለገሉት ሽማግሌዎች ጋራ ተማከረ፤ “ለዚህ ሕዝብ ምን መልስ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” አላቸው።
7እነርሱም፣ “ለዚህ ሕዝብ ደግ ከሆንህለት፣ ደስ ካሠኘኸውና የሚስማማውን መልስ ከሰጠኸው ምን ጊዜም አገልጋይህ ይሆናል” ብለው መለሱለት።
8ሮብዓም ግን ሽማግሌዎች የሰጡትን ምክር ንቆ፣ ዐብሮ አደጎቹና አገልጋዮቹ ከሆኑት ወጣቶች ምክር ጠየቀ፤ 9እንዲህም አላቸው፤ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚሉኝ ለእነዚህ ሰዎች የምትሰጡኝ ምክር ምንድን ነው? ምንስ ብለን እንመልስላቸው?”
10ዐብሮ አደጎቹም ወጣቶች እንዲህ አሉት፤ “ ‘አባትህ በላያችን ከባድ ቀንበር ጫነብን፤ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚሉህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ይልቅ ትወፍራለች፤ 11አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ”
12ንጉሡ፣ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት፣ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም ተመልሰው መጡ። 13ንጉሡ ሮብዓምም በሽማግሌዎቹ የተሰጠውን ምክር ንቆ ሕዝቡን የሚያስከፋ መልስ ሰጣቸው፤ 14እርሱም ወጣቶቹ በሰጡት ምክር መሠረት፣ “አባቴ ቀንበራችሁን አከበደባችሁ፤ እኔ ደግሞ የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” አላቸው። 15እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአኪያ አማካይነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ስለ ወሰነ፣ ንጉሡ ሕዝቡን አላዳመጠም።
16መላው እስራኤልም ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤
“ከዳዊት ምን ድርሻ አለን?
ከእሴይስ ልጅ ምን ክፍል አለን?
እስራኤል፣ ሆይ፤ ወደ ድንኳንህ ተመለስ፤
ዳዊት ሆይ፤ አንተም የገዛ ቤትህን ጠብቅ።”
ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ የቤታቸው ተመለሱ። 17ይሁን እንጂ ሮብዓምም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ነገሠ።
18ንጉሥ ሮብዓም የጕልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ። 19ስለዚህ እስራኤል እስከ ዛሬ ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፀ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ