1 ጢሞቴዎስ 6:1-10

1 ጢሞቴዎስ 6:1-10 NASV

የእግዚአብሔር ስምና ትምህርቱም እንዳይሰደቡ፣ በባርነት ቀንበር ሥር ያሉ ሁሉ፣ ጌቶቻቸው ሙሉ ክብር እንደሚገባቸው አድርገው ይቍጠሩ። የሚያምኑ ጌቶች ያሏቸውም፣ ወንድሞች ስለ ሆኑ የሚገባቸውን ክብር አይንፈጓቸው፤ ይልቁንም በአገልግሎታቸው የሚጠቀሙ አማኞችና ወዳጆቻቸው ስለ ሆኑ የበለጠ ሊያገለግሏቸው ይገባል። እነዚህን ነገሮች አስተምር፤ ምከርም። ማንም የሐሰት ትምህርት ቢያስተምር፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጤናማ ቃልና እውነተኛ መንፈሳዊነትን ከሚያጐለብት ትምህርት ጋራ የማይስማማ ቢሆን፣ ያ ሰው በትዕቢት ተወጥሯል፤ አንዳችም አያስተውልም። ስለ ቃላት ለመከራከርና ለመጣላት ክፉ ጕጕት አለው፤ እነዚህም ቅናትን፣ ጥልን፣ ስድብን፣ መጥፎ ጥርጣሬን ያስከትላሉ፤ እውነትን በተቀሙና መንፈሳዊው ነገር ትርፍ ማግኛ በሚመስላቸው፣ አእምሮ በጐደላቸው ሰዎችም መካከል የማያባራ ንትርክ ያመጣሉ። ነገር ግን እውነተኛ መንፈሳዊነት ባለን ነገር ከመርካት ጋራ ትልቅ ትርፍ ነው። ምክንያቱም ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። ነገር ግን ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል። ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ። ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው። አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጕጕት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።