1 ጢሞቴዎስ 5:17-25

1 ጢሞቴዎስ 5:17-25 NASV

ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ የሚያስተዳድሩ፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚተጉ ሽማግሌዎች ዕጥፍ ክብር ይገባቸዋል፤ መጽሐፍም፣ “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር፤” ደግሞም፣ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” ይላልና። በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ካልተደገፈ በቀር በሽማግሌ ላይ የሚቀርብ ክስ አትቀበል። ሌሎች አይተው እንዲጠነቀቁ ኀጢአት የሚሠሩትን በጉባኤ ፊት ገሥጻቸው። በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በተመረጡትም መላእክት ፊት እነዚህን ትእዛዞች ያለ አድልዎ እንድትጠብቅና አንዳችም ነገር በማበላለጥ እንዳታደርግ ዐደራ እልሃለሁ። በማንም ላይ እጅ ለመጫን አትቸኵል፤ ከሌሎችም ጋራ በኀጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ። ለሆድህና ደጋግሞ ለሚነሣብህ ሕመም፣ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣበት እንጂ ከእንግዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ። የአንዳንድ ሰዎች ኀጢአት ግልጽ ነው፤ ከእነርሱም ቀድሞ ፍርድ ቦታ ይደርሳል፤ ሌሎችን ግን ኀጢአታቸው ይከተላቸዋል። መልካም ሥራም እንደዚሁ ግልጽ ነው፤ ግልጽ ያልሆነ ቢኖርም እንኳ ተሰውሮ አይቀርም።