1 ሳሙኤል 6
6
የታቦቱ ወደ እስራኤል መመለስ
1የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን ግዛት ሰባት ወር ቈየ። 2ፍልስጥኤማውያን ካህናትንና ጠንቋዮችን ጠርተው፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት ምን እናድርገው? ወደ ስፍራው እንዴት መመለስ እንደሚገባን ንገሩን” አሏቸው።
3እነርሱም፣ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ከበደል መሥዋዕት ጋራ ስደዱት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፤ በዚያ ጊዜ ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ ላይ ለምን እንዳልተነሣ ታውቃላችሁ” አሏቸው።
4ፍልስጥኤማውያንም፣ “የምንልከው የበደል መሥዋዕት ምን መሆን አለበት?” ሲሉ ጠየቁ።
እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “እናንተንም ሆነ አለቆቻችሁን የመታው መቅሠፍት አንድ ዐይነት በመሆኑ፣ በፍልስጥኤማውያን ገዦች ቍጥር ልክ ዐምስት የወርቅ ዕባጮችና ዐምስት የወርቅ ዐይጦች ላኩ። 5አገሩን በማጥፋት ላይ ባሉት ዕባጮችና ዐይጦች ዐይነት ምስሎችን ሠርታችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብር ስጡ። ይህን ካደረጋችሁ እጁን ከእናንተ፣ ከአማልክታችሁና ከምድራችሁ ላይ ያነሣ ይሆናል። 6እንደ ግብጻውያንና እንደ ፈርዖን ልባችሁን የምታደነድኑት ለምንድን ነው? እነርሱም እስራኤላውያንን የለቀቋቸው እርሱ በጽኑ ከቀጣቸው በኋላ አይደለምን?
7“ስለዚህ አዲስ ሠረገላና ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት የሚያጠቡ ላሞች አዘጋጁ። ላሞቹን በሠረገላው ጥመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውን ግን ወደ ቤት መልሷቸው። 8የእግዚአብሔርን ታቦት ወስዳችሁ በሠረገላው ላይ አኑሩ፤ በታቦቱም አጠገብ ባለው ሣጥን ውስጥ ለበደል መሥዋዕት የምትልኩትን የወርቅ ምስሎች አስቀምጡ፤ በፈለገውም መንገድ እንዲሄድ ልቀቁት፤ 9ነገር ግን ወዴት እንደሚሄድ ተመልከቱ፤ ወደ ቤትሳሚስ አቅጣጫ ወደ ገዛ አገሩ የሚሄድ ከሆነ፣ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው። ወደዚያ ካልሄደ ግን፣ መከራው በአጋጣሚ የደረሰብን እንጂ የርሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን።”
10እነርሱም እንደዚሁ አደረጉ። ሁለቱን ላሞች ወስደው በሠረገላው ጠመዷቸው፤ እንቦሶቻቸውንም በቤት ውስጥ ዘጉባቸው። 11የእግዚአብሔርንም ታቦት፣ የወርቁን ዐይጦችና የዕባጮቹን ምስሎች በሠረገላው ላይ ጫኑ። 12ከዚያም ላሞቹ መንገዳቸውን ይዘው እምቧ እምቧ እያሉ ቀጥ ብለው ወደ ቤትሳሚስ አመሩ። የፍልስጥኤም ገዦችም እስከ ቤትሳሚስ ድንበር ተከተሏቸው።
13በዚህ ጊዜ የቤትሳሚስ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ስንዴአቸውን ያጭዱ ነበር፤ ቀና ብለው ሲመለከቱም ታቦቱን በማየታቸው በጣም ደስ አላቸው። 14ሠረገላውም ወደ ቤትሳሚስ ወደ ኢያሱ ዕርሻ መጥቶ በአንድ ትልቅ ቋጥኝ አጠገብ ቆመ። ሕዝቡም የሠረገላውን ዕንጨት ፈልጠው፣ ሁለቱን ላሞች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 15ሌዋውያኑም የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የወርቅ ዕቃዎቹን ከያዘው ሣጥን ጋራ አውርደው በትልቁ ድንጋይ ላይ አኖሩ። በዚያችም ዕለት የቤትሳሚስ ሕዝብ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ መሥዋዕቶችንም ሠዉ። 16ዐምስቱ የፍልስጥኤም ገዦችም ይህን ሁሉ ካዩ በኋላ በዚያ ዕለት ወደ አቃሮን ተመለሱ።
17ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የላኳቸው የወርቅ ዕባጮች አንዱ ስለ አሽዶድ፣ አንዱ ስለ ጋዛ፣ አንዱ ስለ አስቀሎና፣ አንዱ ስለ ጋትና አንዱ ስለ አቃሮን የቀረቡ ናቸው፤ 18የወርቅ ዐይጦቹም ቍጥር፣ ዐምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች በሚያስተዳድሯቸው የተመሸጉ ከተሞችና ከእነዚህ ውጭ ባሉት መንደሮቻቸው ቍጥር ልክ ነው። በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ ዕርሻ ውስጥ የእግዚአብሔርን ታቦት ያስቀመጡበት ያ ትልቅ ድንጋይ እስከ ዛሬ ምስክር ነው።
19ነገር ግን እግዚአብሔር ከቤትሳሚስ ሰዎች ጥቂቱን መታ፤ ወደ እግዚአብሔር ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና ከመካከላቸው ሰባ#6፥19 ጥቂት የዕብራይስጥ ቅጆች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆችና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን 50,070 ይላል። ሰዎችን ገደለ፤ እግዚአብሔር እጅግ ስለ መታቸውም ሕዝቡ አለቀሰ። 20የቤትሳሚስም ሰዎች፣ “ታዲያ በዚህ ቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ማን መቆም ይችላል? ታቦቱስ ከዚህ ወጥቶ ወደ ማን ይሂድ?” አሉ።
21ከዚያም ወደ ቂርያትይዓይሪም ሰዎች መልእክተኞች ልከው፣ “ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰውልናል፤ ውረዱና ይዛችሁ ወደ ሰፈራችሁ ውጡ” አሏቸው።
Currently Selected:
1 ሳሙኤል 6: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.