ስለዚህ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ወደ ቦሦር ወንዝ መጡ፤ ጥቂቶቹም በቦሦር ወንዝ ቈዩ፤ ሁለት መቶዎቹ እጅግ ዝለው ስለ ነበር ወንዙን መሻገር አልቻሉምና። ነገር ግን ዳዊትና አራት መቶ ሰዎች መከታተላቸውን ቀጠሉ። እነርሱም በምድረ በዳ አንድ ግብፃዊ አገኙ፤ ወደ ዳዊትም አመጡት፤ የሚጠጣውን ውሃና የሚበላውን ምግብ ሰጡት። እንደዚሁም የበለስ ጥፍጥፍ ቍራሽና ሁለት ደረቅ የወይን ዘለላዎች ሰጡት። ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም እህል ስላልበላ፣ ውሃም ስላልጠጣ ይህን ከበላ በኋላ ነፍሱ ተመለሰች። ዳዊትም፣ “አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔ ግብፃዊ ስሆን፣ የአንድ አማሌቃዊ ባሪያ ነኝ፤ ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ በነበረበት ጊዜ ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። የከሊታውያንን ደቡብ፣ የይሁዳን ግዛትና የካሌብን ደቡብ ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።” ዳዊትም፣ “ታዲያ ወራሪው ሰራዊት ወዳለበት መርተህ ታደርሰኛለህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እንደማትገድለኝ ወይም ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ እንጂ እነዚህ ወራሪዎች ወዳሉበት አደርስሃለሁ” አለው። ዳዊትን ወደ ታች መርቶ ባደረሰው ጊዜም፣ ወራሪዎቹ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሣ በየቦታው ተበታትነው ይበሉ፣ ይጠጡና ይዘፍኑ፣ ይጨፍሩም ነበር። ዳዊት፣ ከዚያች ዕለት ማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ምሽት ድረስ ወጋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር፣ ከመካከላቸው ያመለጠ አንድም አልነበረም። ዳዊት አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፣ ሁለቱንም ሚስቶቹን አስመለሰ። ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች፣ ምርኮም ሆነ ሌላ፣ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጐደለ አልነበረም፤ ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ።
1 ሳሙኤል 30 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 30
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 30:9-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos