1 ሳሙኤል 27
27
ዳዊት በፍልስጥኤማውያን መካከል መኖሩ
1ዳዊት ግን በልቡ፣ “ከእነዚህ ቀናት በአንዱ በሳኦል እጅ መገደሌ ስለማይቀር፣ የሚበጀኝ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር መሸሽ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላም ሳኦል በእስራኤል ሁሉ እኔን ማሳደዱን ይተዋል፤ እኔም ከእጁ አመልጣለሁ” ብሎ ዐሰበ።
2ስለዚህ ዳዊትና አብረውት ያሉት ስድስት መቶ ሰዎች ተነሥተው የጌት ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ ሄዱ። 3ዳዊትና ሰዎቹ በጌት በአንኩስ ዘንድ ተቀመጡ፤ እያንዳንዱ ሰው ከቤተ ሰቡ ጋር ነበረ፤ ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ጋር፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የናባል ሚስት ከነበረችው ከቀርሜሎሳዊቷ አቢግያ ጋር ነበር። 4ሳኦልም፣ ዳዊት ወደ ጌት እንደ ሸሸ በሰማ ጊዜ፣ እርሱን ማሳደዱን ተወ።
5ከዚያም ዳዊት አንኩስን፣ “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ በአገሪቱ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ እኖር ዘንድ ስፍራ ይሰጠኝ፤ ስለ ምን አገልጋይህ ካንተ ጋር በንጉሥ ከተማ ይቀመጣል?” አለው።
6ስለዚህ በዚያ ዕለት አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ጺቅላግም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ ሆነች። 7ዳዊት በፍልስጥኤማውያን ምድር አንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀመጠ።
8በዚያ ጊዜም ዳዊትና ሰዎቹ ወጥተው ጌሹራውያንን፣ ጌርዛውያንንና አማሌቃውያንን ወረሩ። እነዚህ ሕዝቦች ከጥንት ጀምሮ፣ እስከ ሱርና እስከ ግብፅ ባለው ምድር ላይ ይኖሩ ነበር። 9ዳዊትም ምድሪቱን በመታበት ጊዜ፣ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አላስቀረም፤ ነገር ግን በጎችንና ላሞችን፣ አህዮችንና ግመሎችን እንዲሁም ልብሶችን ወሰደ፤ ወደ አንኩስም ተመለሰ።
10አንኩስም፣ “ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ?” ሲል በጠየቀው ጊዜ ዳዊት፣ “የዘመትነው በይሁዳ ደቡብ፣ ወይም በይረሕምኤላውያን ደቡብ፣ ወይም በቄናውያን ደቡብ ላይ ነው” በማለት ይመልስ ነበር። 11ዳዊት “ ‘እርሱ እንዲህ አድርጓል’ ብለው ይነግሩብናል” ብሎ ስላሰበ፣ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አስቀርቶ ወደ ጌት አላመጣም። በፍልስጥኤም ግዛት በኖረበት ዘመን ሁሉ፣ እንዲህ ማድረጉ የተለመደ ነበር። 12አንኩስም በልቡ፣ “እርሱ ራሱ የገዛ ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን እጅግ እንዲጠሉት ስላደረገ፣ ለዘላለም አገልጋዬ ይሆናል” ብሎ ስላሰበ ዳዊትን አመነው።
Currently Selected:
1 ሳሙኤል 27: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.