ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ነገ የወር መባቻ በዓል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን፣ አለመኖርህ ይታወቃል። ከነገ ወዲያ ምሽት ላይ ይህ ችግር በተፈጠረ ዕለት ወደ ተደበቅህበት ስፍራ ሂድና ኤዜል በተባለው ድንጋይ አጠገብ ቈይ። እኔም በአንድ ዒላማ ላይ እንደሚያነጣጥር ሰው ወደ ድንጋዩ አጠገብ ሦስት ፍላጻ እወረውራለሁ፤ ከዚያም፣ ‘ሂድና ፍላጾቹን አምጣቸው’ ብዬ አንድ ልጅ እልካለሁ፤ ልጁንም፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት፣ ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ሄደህ አምጣቸው’ ያልሁት እንደ ሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ክፉ ነገር አያገኝህም፤ አደጋም የለም፤ ውጣና ና። ነገር ግን ልጁን፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት ከአንተ ወዲያ ዐልፎ ነው’ ያልሁት እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንድትሄድ ፈቅዷልና ሂድ። አንተና እኔ ስለ ተነጋገርነው ነገር እነሆ፤ እግዚአብሔር በመካከላችን ለዘላለም ምስክር ነው።” ስለዚህም ዳዊት በዱር ተደበቀ፤ የወር መባቻ በዓል በተከበረበት ጊዜ፣ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ፤ ንጉሡ እንደ ወትሮው በግድግዳው አጠገብ ተቀመጠ፤ ዮናታን ከፊት ለፊቱ፣ አበኔር ደግሞ ከአጠገቡ ተቀመጡ፤ የዳዊት መቀመጫ ግን ባዶ ነበር። ሳኦልም፣ “ዳዊት በሥርዐቱ መሠረት እንዳይነጻ የሚያደርገው አንድ ነገር ገጥሞታል፤ በርግጥም አልነጻም” ብሎ ስላሰበ፣ በዚያ ቀን ምንም አልተናገረም። በማግስቱም፣ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን የዳዊት መቀመጫ ባዶ ነበር፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ዮናታንን፣ “የእሴይ ልጅ ትናንትናም፣ ዛሬም ግብር ላይ ያልተገኘው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ዮናታንም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም እንዲሄድ እፈቅድለት ዘንድ አጥብቆ ለመነኝ። እርሱም ‘ቤተ ሰባችን በከተማዪቱ ውስጥ መሥዋዕት ስለሚያደርግ በዚያ እንድገኝ ወንድሜ አዞኛልና ልሂድ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ወንድሞቼን ለማየት እንድሄድ አሰናብተኝ’ አለኝ። በንጉሡ ግብር ላይ ሳይገኝ የቀረውም በዚህ ምክንያት ነው።” ሳኦል በዮናታን ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አንተ የዚያች ጠማማና ዐመፀኛ ሴት ልጅ! ለአንተው ለራስህ ውርደት፣ ለወላጅ እናትህም ዕፍረት ከሚሆነው ከእሴይ ልጅ ጋራ መግጠምህን የማላውቅ መሰለህ? የእሴይ ልጅ በምድር ላይ በሕይወት እስካለ ድረስ አንተም ሆንህ መንግሥትህ አትጸኑም። መሞት ስለሚገባው፣ ሰው ላክና አስመጣልኝ!” ዮናታንም፣ “ለምን ይገደላል? ጥፋቱስ ምንድን ነው?” ሲል አባቱን ጠየቀ። ሳኦልም ዮናታንን ለመግደል ጦሩን ወረወረበት። ስለዚህ ዮናታን፣ አባቱ ዳዊትን ለመግደል ቈርጦ መነሣቱን ዐወቀ። ዮናታንም በታላቅ ቍጣ ከግብሩ ላይ ተነሣ፤ አባቱም ዳዊትን ስላዋረደው ወሩ በገባ በሁለተኛው ቀን ምግብ አልበላም። በማግስቱም ጧት ዮናታን አንድ ትንሽ ልጅ አስከትሎ፣ ከዳዊት ጋራ ወደ ተቃጠረበት ቦታ ሄደ፤ ልጁንም፣ “ሩጥ! የምሰዳቸውን ፍላጻዎች ፈልጋቸው” አለው፤ ልጁም በሮጠ ጊዜ፣ ከርሱ አሳልፎ አንድ ፍላጻ ወረወረ። ልጁም የዮናታን ፍላጻ ባረፈበት ስፍራ እንደ ደረሰ፤ ዮናታን ጠራውና፣ “ፍላጻው ካንተ ወዲያ ዐልፎ የለምን?” አለው። እርሱም “ቶሎ በል! ፍጠን! አትቁም!” ሲል ጮኸበት፤ ልጁም ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው ተመለሰ። ከዮናታንና ከዳዊት በቀር ልጁ ስለዚህ ነገር የሚያውቀው አንዳች አልነበረም። ከዚያም ዮናታን የጦር መሣሪያውን ለልጁ ሰጥቶ፣ “ይዘህ ወደ ከተማ ተመለስ” አለው። ልጁ ከሄደ በኋላ፣ ዳዊት ከድንጋዩ በስተ ደቡብ ከተደበቀበት ቦታ ወጥቶ በዮናታን ፊት ሦስት ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደለት፤ ከዚያም ተሳሳሙ፤ ተላቀሱም፤ በይበልጥ ያለቀሰው ግን ዳዊት ነበር። ዮናታንም ዳዊትን፤ “ ‘በአንተና በእኔ፣ በዘሮችህና በዘሮቼ መካከል እግዚአብሔር ለዘላለም ምስክር ነው’ ተባብለን ወዳጅነታችን እንዲጸና በእግዚአብሔር ስም ስለ ተማማልን እንግዲህ በሰላም ሂድ” አለው። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ተመለሰ።
1 ሳሙኤል 20 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 20
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 20:18-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች