የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 2:1-10

1 ሳሙኤል 2:1-10 NASV

ሐናም እንዲህ ብላ ጸለየች፤ “ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፤ ቀንዴም በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፤ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህ ደስ ይለኛልና። “እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ ማንም የለም፤ ከአንተም በቀር ሌላ የለም፤ እንደ አምላካችን ያለ ዐለት የለም። “ይህን ያህል በመታበይ አትናገሩ፤ እንዲህ ያለውም የእብሪት ቃል ከአፋችሁ አይውጣ፤ እግዚአብሔር አምላክ ዐዋቂ ነውና፤ ሥራም ሁሉ በእርሱ ይመዘናል። “የኀያላን ቀስቶች ተሰባብረዋል፤ ደካሞች ግን በኀይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ ለእንጀራ ሲሉ ተገዙ፤ ተርበው የነበሩ ግን እንጀራ ጠገቡ፤ መካኒቱ ሰባት ልጆች ወልዳለች፤ ብዙ ወንዶች ልጆች ወልዳ የነበረችው ግን መከነች። “እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤ ወደ መቃብር ያወርዳል፤ ያወጣልም። እግዚአብሔር ያደኸያል፤ ያበለጽጋልም፤ ያዋርዳል፤ ከፍ ከፍም ያደርጋል። እርሱ ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤ ምስኪኑንም ከጕድፍ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ከመኳንንቱ ጋር ያስቀምጣቸዋል፤ የክብር ዙፋንም ያወርሳቸዋል። “የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፣ ዓለምን በእነርሱ ላይ አድርጓል። እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል፤ ክፉዎች ግን በጨለማ ውስጥ ይጣላሉ። “ሰው በኀይሉ ድል አያደርግም፤ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ፤ እርሱ ከሰማይ ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል።