ፍልስጥኤማውያን ሰራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፣ በይሁዳ ምድር በሰኰት ላይ አከማቹ፤ እነርሱም በሰኰትና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌሰደሚም ሰፈሩ። ሳኦልና እስራኤላውያን ተሰብስበው፣ በዔላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ቦታ ቦታቸውን ያዙ። ሸለቆ በመካከላቸው ሆኖ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ኰረብታ እስራኤላውያን ደግሞ፣ ሌላውን ኰረብታ ያዙ። ከጌት የመጣ ቁመቱ ከዘጠኝ ጫማ በላይ የሆነ፣ ጎልያድ የተባለ አንድ ጀግና ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ። እርሱም ከናስ የተሠራ የራስ ቍር ደፍቶ፣ ክብደቱ አምስት ሺሕ ሰቅል የሆነ የናስ ጥሩር ለብሶ ነበር። በእግሮቹ ላይ የናስ ገምባሌ አድርጎ፣ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናስ ጭሬ ይዞ ነበር። የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፣ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሰራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለ ምንድን ነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፣ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤ ከእኔ ጋር ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፣ እኛ ባሪያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባሪያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።” ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፣ “ዛሬ የእስራኤልን ሰራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ። ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም። ዳዊት በይሁዳ የቤተ ልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤልያብ፣ ሁለተኛው አሚናዳብ፣ ሦስተኛውም ሣማ ይባላሉ፤ ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጧትና ማታ ፊት ለፊት ብቅ እያለ ቆሞ ይታያቸው ነበር። በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ። ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለክፍል አዛዣቸው አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደ ሆኑ አይተህ፣ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ። እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው በዔላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ናቸው።” ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፣ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጕዞ ጀመረ። ልክ ሰራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ። እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሀት ከፊቱ ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፣ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር። ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፣ “ለመሆኑ ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፣ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ፣ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልም?” አለ። ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፣ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን፣ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ ባሪያህ ሄዶ ይዋጋዋል” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፣ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለሆነ፣ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፣ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፣ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጕረሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባሪያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም፣ “ሂድ፤ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን” አለው። ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ጥሩር አጠለቀለት፤ ከናስ የተሠራ ቍርም ደፋለት። ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፣ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤ እርሱም ሳኦልን፣ “ያልተለማመድሁት ስለሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ሁሉንም አወለቀው። ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፣ ወንጭፉን በእጁ ይዞ፣ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። እርሱም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። እርሱም፣ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቈርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፣ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፣ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ፍልስጥኤማዊውም በግምባሩ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዝዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ። ከዚህ በኋላ የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እየፎከሩ ፍልስጥኤማውያንን እስከ ጌት መግቢያና እስከ ዔቅሮን በሮች ድረስ አሳደዷቸው። የፍልስጥኤማውያንም ሬሳ ከሸዓይራይም አንሥቶ እስከ ጌት ከዚያም እስከ ዔቅሮን በሮች ባለው መንገድ ላይ ወድቆ ነበር። እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሱ፤ ሰፈራቸውንም በዘበዙ። ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማዊውን የጦር መሣሪያዎች በራሱ ድንኳን ውስጥ አስቀመጠ። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ለመግጠም በሚሄድበት ጊዜ ሳኦል ተመልክቶ የሰራዊቱን አዛዥ አበኔርን፣ “አበኔር ሆይ፤ ይህ ልጅ የማን ነው?” ሲል ጠየቀው። አበኔርም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አላውቅም” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፣ “እንግዲህ ወጣቱ የማን ልጅ እንደ ሆነ ተከታትለህ ድረስበት” አለው። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ እንደ ተመለሰ፣ አበኔር ይዞ ንጉሡ ዘንድ አቀረበው። በዚህ ጊዜ ዳዊት የጎልያድን ራስ በእጁ ይዞ ነበር። ሳኦልም፣ “አንተ ወጣት፣ የማን ልጅ ነህ?” ሲል ጠየቀው። ዳዊትም፣ “እኔ የአገልጋይህ የቤተ ልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ ነኝ” ሲል መለሰ።
1 ሳሙኤል 17 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 17
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 17:1-58
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos