1 ሳሙኤል 17:1-51

1 ሳሙኤል 17:1-51 NASV

ፍልስጥኤማውያን ሰራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፣ በይሁዳ ምድር በሦኮን ላይ አከማቹ፤ እነርሱም በሰኰትና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌሰደሚም ሰፈሩ። ሳኦልና እስራኤላውያን ተሰብስበው፣ በኤላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ቦታ ቦታቸውን ያዙ። ሸለቆ በመካከላቸው ሆኖ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ኰረብታ እስራኤላውያን ደግሞ፣ ሌላውን ኰረብታ ያዙ። ከጋት የመጣ ቁመቱ ከዘጠኝ ጫማ በላይ የሆነ፣ ጎልያድ የተባለ አንድ ጀግና ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ። እርሱም ከናስ የተሠራ የራስ ቍር ደፍቶ፣ ክብደቱ ዐምስት ሺሕ ሰቅል የሆነ የናስ ጥሩር ለብሶ ነበር። በእግሮቹ ላይ የናስ ገምባሌ አድርጎ፣ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናስ ጭሬ ይዞ ነበር። የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፣ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሰራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለ ምንድን ነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፣ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤ ከእኔ ጋራ ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፣ እኛ ባሪያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባሪያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።” ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፣ “ዛሬ የእስራኤልን ሰራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ። ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም። ዳዊት በይሁዳ የቤተ ልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤልያብ፣ ሁለተኛው አሚናዳብ፣ ሦስተኛውም ሣማ ይባላሉ፤ ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጧትና ማታ ፊት ለፊት ብቅ እያለ ቆሞ ይታያቸው ነበር። በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን የተጠበሰ ኤፋ እህል፤ ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ። ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለክፍል አዛዣቸው ዐብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደ ሆኑ አይተህ፣ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ። እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋራ ሆነው በኤላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋራ እየተዋጉ ናቸው።” ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፣ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጕዞ ጀመረ። ልክ ሰራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። ከእነርሱም ጋራ በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጋት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ። እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሀት ከፊቱ ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፣ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር። ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፣ “ለመሆኑ ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፣ ዳዊት ከሰዎች ጋራ ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ፣ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልም?” አለ። ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፣ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን፣ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ ባሪያህ ሄዶ ይዋጋዋል” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፣ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለ ሆነ፣ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፣ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፣ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጕረሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባሪያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም፣ “ሂድ፤ እግዚአብሔር ካንተ ጋራ ይሁን” አለው። ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ጥሩር አጠለቀለት፤ ከናስ የተሠራ ቍርም ደፋለት። ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፣ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ። እርሱም ሳኦልን፣ “ያልተለማመድሁት ስለ ሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ሁሉንም አወለቀው። ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ ዐምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኰረጆው ከጨመረ በኋላ፣ ወንጭፉን በእጁ ይዞ፣ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም፣ “እስኪ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት ጌታ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቈርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፣ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፣ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኰረጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ፍልስጥኤማዊውም በግምባሩ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዝዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።