የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 14

14
1አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር።
2ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ መጌዶን በተባለ ስፍራ ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤ 3ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ዮናታን አለመኖሩን ግን ያወቀ ሰው አልነበረም።
4ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ አንዱ ቦጼጽ ሌላው ሴኔ የተባሉ ሁለት ሾጣጣ ዐለቶች ነበሩ። 5አንዱ ዐለት በስተ ሰሜን በኩል በማክማስ አንጻር፣ ሌላው ደግሞ በስተ ደቡብ በኩል በጊብዓ አንጻር ይገኝ ነበር።
6ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና፤ ወደነዚያ ሸለፈታሞች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና” አለው።
7ወጣቱም ጋሻ ጃግሬ፣ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋር ነኝ” አለው።
8ዮናታንም እንዲህ አለው፣ “እንግዲያውስ ና፤ ወደ ሰዎቹ እንሻገርና እንታያቸው። 9እነርሱም፣ ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን’ ካሉን፣ ባለንበት ሆነን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም። 10ነገር ግን፣ ‘ወደ እኛ ውጡ’ ካሉን፣ እግዚአብሔር እነርሱን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ስለሆነ፣ ወደ እነርሱ እንወጣለን።”
11ሁለቱም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ በታዩ ጊዜ፣ ፍልስጥኤማውያን፣ “እነሆ፤ ዕብራውያን ከተደበቁባቸው ጕድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ። 12የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፣ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ አንድ ነገር እናሳያችሁ” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው።
ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፣ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና” አለው።
13ዮናታን በእጁና በእግሩ ተፍጨርጭሮ፣ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተ ኋላው እየተከተለ ገደላቸው። 14ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳይ አንድ ጥማድ በምታውል የዕርሻ ቦታ#14፥14 ዕብራይስጡ ግማሽ ቀንበር ይላል፤ ይኸውም በጥማድ በሬ በአንድ ቀን የሚታረሰውን መሬት የሚያሳይ ነው ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ።
የፍስጥኤማውያን መሸነፍ
15በሰፈር በዕርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተንቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር#14፥15 ወይም ከፍተኛ የሆነ
16በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ዘቦች፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ። 17ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፣ “እስኪ፣ ሰራዊቱን ቍጠሩና ማን ከዚህ እንደ ሄደ እዩ” አላቸው። ይህን ባደረጉ ጊዜም ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም።
18ሳኦልም አኪያን፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ ታቦቱ በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር#14፥18 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን ኤፉዱን ወደዚህ አምጣ፤ በዚያ ጊዜ እርሱ ኤፉዱን በእስራኤል ፊት ለብሶት ነበር ይላል።19ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፣ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፣ “እጅህን መልስ” አለው።
20ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እነርሱም ፍልስጥኤማውያን በሰይፋቸው እየተጨፋጨፉ በታላቅ ትርምስ ላይ ሆነው አገኟቸው። 21እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ገቡ። 22በኰረብታማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፣ አጥብቀው በመከታተል አሳደዷቸው። 23በዚያ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤት አዌን ዘልቆ ሄደ።
ዮናታን ማር በላ
24ሳኦል፣ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አምሎ ስለ ነበር፣ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም።
25ሰራዊቱ#14፥25 ወይም አሁን የምድሩ ነዋሪዎች በሙሉ ሁሉ ወደ ጫካ ሲገባ፣ ማር በመሬቱ ላይ ይታይ ነበር። 26ሕዝቡ ወደ ጫካው በገባ ጊዜ፣ የማሩ ወለላ እየተንጠባጠበ መውረዱን አየ፤ ሆኖም መሐላውን ፈርቶ ስለ ነበር፣ እጁን ወደ አፉ የዘረጋ ማንም አልነበረም። 27ነገር ግን ዮናታን አባቱ ሕዝቡን በመሐላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። ስለዚህ በእጁ የያዘውን ዘንግ ጫፍ በማሩ ወለላ ውስጥ በማስገባት እጁን ወደ አፉ አደረገ፤ ዐይኑም በራ። 28ከዚያም አንዱ ወታደር፣ “አባትህ ሰራዊቱን፣ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!’ በማለት በጽኑ መሐላ አስሯል። ሰው ሁሉ የተዳከመው በዚሁ ምክንያት ነው” አለው።
29ዮናታንም እንዲህ አለ፤ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሯል፤ ከዚህ ማር ጥቂት በቀመስሁ ጊዜ ዐይኔ እንዴት እንደ በራ ተመልከቱ።#14፥29 ወይም ኀይሌ እንዴት እንደ ታደሰ 30ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው እጅ ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፤ የተገደሉትም ፍልስጥኤማውያን ቍጥር ከዚህ በበለጠ ነበር።”
31በዚያች ዕለት እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ ከመቷቸው በኋላ እጅግ ዝለው ነበር። 32በምርኮው ላይ ተረባርበው በጉን፣ በሬውንና ጥጃውን በመውሰድ በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት። 33ከዚያም ለሳኦል፣ “እነሆ፤ ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን እየበደለ ነው” ተብሎ ተነገረው።
ሳኦልም፣ “ሕግ ተላልፋችኋል፤ በሉ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አቅርቡልኝ” አለ። 34እርሱም፣ “በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ፣ ‘እያንዳንዳችሁ በሬዎቻችሁንና በጎቻችሁን አምጡ፤ እዚሁ ዐርዳችሁ ብሉ፤ ነገር ግን ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን አትበድሉ’ በሏቸው” አለ።
ስለዚህ በዚያች ሌሊት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ ዐረደው። 35ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያ ሲሠራም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።
36ሳኦልም፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትለን በሌሊት እንውረድና እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት አናስቀርላቸው” አለ።
እነርሱም፣ “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” ብለው መለሱለት።
ካህኑ ግን፣ “እዚሁ እግዚአብሔርን እንጠይቅ” አለ።
37በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትዬ ልውረድን? በእስራኤላውያንስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያች ቀን አልመለሰለትም።
38ስለዚህ ሳኦል እንዲህ አለ፤ “የሰራዊቱ መሪዎች ሁላችሁም ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ምን ኀጢአት እንደ ተሠራ እንወቅ። 39እስራኤልን የታደገ ሕያው እግዚአብሔርን አድራጊው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን መሞት አለበት።” ነገር ግን ከሕዝቡ መካከል የመለሰለት አንድም አልነበረም።
40ሳኦልም እስራኤላውያንን ሁሉ፣ “እናንተ በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው።
ሰዎቹም፣ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ብለው መለሱለት።
41ከዚያ በኋላ ሳኦል፣ “ትክክለኛውን መልስ ስጠኝ”#14፥41 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን ዛሬ ለባሪያህ ያልመለስህለት ለምንድን ነው? ጥፋቱ በእኔና በልጄ በዮናታን ላይ ከሆነ በኡሪም መልስልን፤ ነገር ግን ጥፋቱ በእስራኤል ሰዎች ላይ ከሆነ በቱሚም መልስ ይላል። ሲል ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ዕጣው በሳኦልና በዮናታን ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ። 42ሳኦልም፣ “በእኔና በልጄ በዮናታን መካከልም ዕጣ ጣሉ” አላቸው። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወደቀ።
43ከዚያም ሳኦል ዮናታንን፣ “እስቲ ያደረግኸውን ንገረኝ” አለው።
ዮናታንም፣ “በዘንጌ ጫፍ ጥቂት ማር ቀምሻለሁ፤ እነሆ፤ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው።
44ሳኦልም፣ “ዮናታን፣ አንተ ካልተገደልህ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፣ የከፋም ነገር ያምጣብኝ” አለ።
45ሕዝቡ ግን ሳኦልን፣ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘ ዮናታን መሞት ይገባዋልን? አይደረግም! ዛሬ ይህን ያደረገው በእግዚአብሔር ርዳታ ስለሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ከራስ ጠጕሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አሉት። ስለዚህ ሰዎቹ ዮናታንን ታደጉት፤ እርሱም ከመሞት ዳነ።
46ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሰ፤ እነርሱም ወደ አገራቸው ተመለሱ።
47ሳኦል በእስራኤል ላይ በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ፣ በዙሪያው ያሉትን ጠላቶቹን ማለትም ሞዓብን፣ አሞናውያንን፣ ኤዶምን፣ የሱባን ነገሥታትና#14፥47 የማሶሬ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሙት ባሕር ጥቅልልና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን ንጉሥ ይላል። ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው። በሄደበት ሁሉ ድል ይነሣ#14፥47 ዕብራይስጡ ያሠቃያቸው ነበር ሲል፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ደግሞ ድል ይነሣቸው ነበር ይላል። ነበር። 48በጀግንነት ተዋግቶ አማሌቃውያንን አሸነፈ፤ እስራኤልንም ይዘርፏቸው ከነበሩት እጅ ታደጋቸው።
የሳኦል ቤተ ሰብ
49የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፣ የሱዊ፣ ሜልኪሳ ነበሩ፤ ሴቶች ልጆቹም ትልቋ ሜሮብ፣ ትንሿ ሜልኮል ይባሉ ነበር። 50የሳኦል ሚስት አኪናሆም የምትባል የአኪማአስ ልጅ ነበረች፤ የሰራዊቱም አዛዥ አበኔር የሚባል የአጎቱ የኔር ልጅ ነበረ። 51የሳኦል አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር ሁለቱም የአቢኤል ልጆች ነበሩ።
52በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከባድ ጦርነት ነበረ፤ ስለዚህ ሳኦል ብርቱ ወይም ጀግና ሰው ባየ ቍጥር ወደ ራሱ ወስዶ እንዲያገለግለው ያደርግ ነበር።

Currently Selected:

1 ሳሙኤል 14: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ