1 ነገሥት 3
3
ሰሎሞን ጥበብን ከእግዚአብሔር መለመኑ
3፥4-15 ተጓ ምብ – 2ዜና 1፥2-13
1ሰሎሞን የግብፅ ንጉሥ የፈርዖን ወዳጅ ሆነ፤ የፈርዖንንም ልጅ አገባ። እርሱም ቤተ መንግሥቱን፣ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ቅጥር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አስቀመጣት።
2በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ስም ገና ቤተ መቅደስ ስላልተሠራ፣ ሕዝቡ አሁንም መሥዋዕት የሚያቀርበው በማምለኪያ ኰረብታ ላይ ነበር። 3ሰሎሞን እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፤ በአባቱ በዳዊት ሥርዐትም ይሄድ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ በኰረብታዎች ላይ መሥዋዕት ይሠዋና ዕጣን ያጥን ነበር።
4ከሁሉ የሚበልጠው የማምለኪያ ኰረብታ ገባዖን ስለ ነበረ፣ ንጉሡ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። ሰሎሞን በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺሕ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። 5በገባዖንም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ አምላክም፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ለምን” አለው።
6ሰሎሞን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አባቴ ዳዊት በእውነት፣ በጽድቅና በቅን ልቦና በፊትህ ስለ ተመላለሰ፣ ለባሪያህ ታላቅ ቸርነትን አሳይተኸዋል፤ ይህ ታላቅ ቸርነት እንዲቀጥል በማድረግ ዛሬም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተኸዋል።
7“እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ባሪያህ በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ እንድነግሥ አድርገሃል፤ እኔ ግን ገና ትንሽ ልጅ ስለሆንሁ፣ መውጫና መግቢያዬን አላውቅም። 8ባሪያህ አንተ በመረጥኸው ሕዝብ፣ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ታላቅ ሕዝብ መካከል ይገኛል። 9ስለዚህ መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው፤ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊያስተዳድር ይችላል?”
10ሰሎሞን ይህን በመለመኑ ጌታ ደስ አለው፤ 11ስለዚህ እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረዥም ዕድሜ፣ ብልጽግና እንድታገኝ ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ ሳይሆን፣ በትክክል ማስተዳደር እንድትችል ማስተዋልን ስለ ጠየቅህ፣ 12ይህንኑ አደርግልሃለሁ፤ ከአንተ በፊት ማንም ያልነበረውን፣ ከአንተም በኋላ ማንም የማያገኘውን ጥበብና አስተዋይ ልቡና እሰጥሃለሁ፤ 13ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅኸውን ብልጽግናና ክብር እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በሕይወት ዘመንህ የሚተካከልህ ማንም ንጉሥ እንዳይኖር ነው። 14አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድ፣ ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትጠብቅ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።” 15ሰሎሞንም ከእንቅልፉ ነቃ፤ እነሆ ሕልም መሆኑን ተረዳ።
ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ፣ በጌታ ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት#3፥15 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። አቀረበ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብዣ አደረገ።
ጥበብን የተሞላ ፍትሕ
16በዚህን ጊዜ ሁለት ዝሙት ዐዳሪዎች ወደ ንጉሡ መጥተው ከፊቱ ቆሙ። 17ከእነርሱም አንዲቱ እንዲህ አለች፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን እንኖራለን፤ አብራኝ እያለችም እኔ ልጅ ወለድሁ፤ 18እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላም፣ ይህች ሴት ወለደች፤ የነበርነው እኛ ብቻ ነን፤ ከሁለታችን በቀር በዚያ ቤት ማንም አልነበረም።
19“የዚህች ሴት ሕፃን ልጅ ስለ ተኛችበት ሌሊት ሞተ። 20ስለዚህም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፣ እኔ አገልጋይህ ተኝቼ ሳለሁ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደችው፤ ከዚያም የእኔን ልጅ ራሷ ታቅፋ፣ የሞተ ልጇን አምጥታ በዕቅፌ አደረገችው። 21በማግስቱም ልጄን ላጠባ ስነሣ እነሆ ሞቷል፤ ነገር ግን በማለዳ ብርሃን ትክ ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድሁት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብሁ።”
22ሌላዪቱም ሴት፣ “ነገሩ አንቺ እንደምትዪው አይደለም፤ የሞተው የአንቺ፣ በሕይወት ያለውም የእኔ ነው” አለች።
የመጀመሪያዋ ሴት ግን አጠንክራ፣ “አይደለም! የሞተው የአንቺ፣ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው” አለች፤ በዚህ ሁኔታም በንጉሡ ፊት ተከራከሩ።
23ንጉሡም፣ “ይህችኛዪቱ፣ ‘የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው፣ የአንቺ የሞተው ነው’ ትላለች፤ ያችኛዪቱ ደግሞ፣ ‘አይደለም የአንቺ ልጅ ሞቷል፣ በሕይወት ያለው የእኔ ነው’ ትላለች” አለ።
24ከዚያም ንጉሡ፣ “እንግዲያውስ ሰይፍ አምጡልኝ” አለ፤ ለንጉሡም ሰይፍ አመጡለት። 25በዚህ ጊዜ ንጉሡ፣ “በሉ በሕይወት ያለውን ልጅ ከሁለት ክፈሉና ለአንዷ ግማሹን፣ ለሌላዪቱም ግማሹን ስጡ” ብሎ አዘዘ።
26በሕይወት ያለው ልጅ እናት ለልጇ እጅግ ስለ ራራች ንጉሡን፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እባክህ በሕይወት ያለውን ሕፃን ለእርሷ ስጣት፤ አትግደለው” አለች።
ሌላዪቱ ግን፣ “ለእኔም ሆነ ለአንቺ አይሰጥም፤ ሁለት ላይ ይከፈል!” አለች።
27ከዚህ በኋላ ንጉሡ፣ “በሉ በሕይወት ያለውን ሕፃን ለመጀመሪያዪቱ ሴት ስጧት፤ አትግደሉት፤ እናቱ እርሷ ናት” አለ።
28እስራኤላውያን ሁሉ ንጉሡ የሰጠውን ፍርድ ሲሰሙ ፈሩት፤ ፍትሕ ለመስጠት የአምላክን ጥበብ የታደለ መሆኑን አይተዋልና።
Currently Selected:
1 ነገሥት 3: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.