የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ነገሥት 17:8-16

1 ነገሥት 17:8-16 NASV

ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፤ “ተነሥና ሲዶና ውስጥ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሄደህ ተቀመጥ፤ በዚያም አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ።” ስለዚህ ተነሥቶ ወደ ሰራፕታ ሄደ። ወደ ከተማዪቱ በር እንደ ደረሰም፣ አንዲት መበለት ጭራሮ ስትለቃቅም አገኛት፤ ጠርቶም፣ “የምጠጣው ውሃ በዕቃ ታመጪልኛለሽን?” ሲል ለመናት። ልታመጣለት ስትሄድ አሁንም ጠራትና፣ “እባክሽን፣ ቍራሽ እንጀራም ይዘሽልኝ ነይ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ዕፍኝ ዱቄትና በማሰሮ ካለው ጥቂት ዘይት በቀር ምንም የለኝም። እነሆ፤ ለራሴና ለልጄ ምግብ አዘጋጅቼ በልተን እንድንሞት ጭራሮ ለቃቅሜ ወደ ቤት ልወስድ ነው” አለችው። ኤልያስም መልሶ እንዲህ አላት፤ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ወደ ቤት ገብተሽ እንዳልሽው አድርጊ፤ በመጀመሪያ ግን ከዚያችው ካለችሽ ትንሽ ዕንጐቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ ከዚያም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር ለምድሪቱ ዝናብ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ፤ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’ ” እርሷም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ በዚህ ሁኔታም ኤልያስ፣ መበለቲቱና ቤተ ሰቧ ብዙ ቀን ተመገቡ፤ በኤልያስ በተነገረው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም ነበርና።