የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ቆሮንቶስ 6:12-20

1 ቆሮንቶስ 6:12-20 NASV

“ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ምንም ነገር በእኔ ላይ አይሠለጥንም። ደግሞም፣ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው። እግዚአብሔር ጌታን ከሙታን እንዳስነሣው፣ እኛንም ደግሞ በኀይሉ ከሙታን ያስነሣናል። ሰውነታችሁ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? ታዲያ፣ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ ከዝሙት ዐዳሪ ሴት ብልቶች ጋር አንድ ላድርገውን? ከቶ አይገባም! ወይስ ከዝሙት ዐዳሪ ጋር የሚተባበር ሰው ከእርሷ ጋር አንድ ሥጋ እንደሚሆን አታውቁምን? “ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ተብሏልና። ነገር ግን ከጌታ ጋር የሚተባበር ከእርሱ ጋር አንድ መንፈስ ይሆናል። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል። ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።