1 ቆሮንቶስ 14:26-40

1 ቆሮንቶስ 14:26-40 NASV

ወንድሞች ሆይ፤ እንግዲህ ምን እንበል? በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው፤ ትምህርት አለው፤ መግለጥ አለው፤ በልሳን መናገር አለው፤ መተርጐም አለው። ይህ ሁሉ ግን ለማነጽ ይሁን። በልሳን የሚናገር ቢኖር፣ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ ሌላው ደግሞ ይተርጕም፤ የሚተረጕም ሰው ከሌለ ግን በጉባኤ መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። ሁለት ወይም ሦስት ነቢያት ይናገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገረውን በጥንቃቄ ይመዝኑ። ከተቀመጡትም መካከል አንድ ሰው አንድ ነገር ቢገለጥለት፣ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። እያንዳንዳችሁ እንድትማሩና እያንዳንዳችሁ እንድትበረታቱ፣ ሁላችሁ በየተራ ትንቢት መናገር ትችላላችሁ። የነቢያት መናፍስት ለነቢያት ይታዘዛሉ፤ እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። በቅዱሳን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲሁ ነው። ሴቶች በጉባኤ ዝም ይበሉ፤ ሕግም እንደሚለው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም፤ ሴቶች ለማወቅ የሚፈልጉት አንዳንድ ነገር ካለ፣ ባሎቻቸውን በቤት ይጠይቁ፤ ምክንያቱም ሴት በጉባኤ መካከል ብትናገር የሚያሳፍር ነው። የእግዚአብሔር ቃል የወጣው ከእናንተ ነውን? ወይስ የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነውን? ማንም ነቢይ ነኝ የሚል ወይም መንፈሳዊ ስጦታ አለኝ የሚል ቢኖር፣ ይህ የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ፤ ይህን የማያውቅ ቢሆን ግን እርሱም አይታወቅ። ስለዚህ፣ ወንድሞች ሆይ፤ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በልሳን መናገርንም አትከልክሉ፤ ነገር ግን ሁሉም በአግባብና በሥርዐት ይሁን።