የሉቃስ ወንጌል 22
22
በኢየሱስ ላይ የተደረገ ሤራ
(ማቴ. 26፥1-5፤ ማር. 14፥1-2፤ ዮሐ. 11፥45-53)
1ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል የሚከበርበት ቀን ተቃርቦ ነበር፤ #ዘፀ. 12፥1-27። 2የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ኢየሱስን ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ በስውር ይፈልጉ ነበር።
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱ
(ማቴ. 26፥14-16፤ ማር. 14፥10-11)
3በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ በሆነው በአስቆሮታዊው ይሁዳ ሰይጣን ገባበት። 4ስለዚህ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደስ ዘብ አዛዦች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ። 5እነርሱም በነገሩ ተደስተው ገንዘብ ሊሰጡት ተዋዋሉ። 6በውሉ ተስማምቶ ሕዝቡ ሳያውቅ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
ኢየሱስ የአይሁድን የፋሲካ ራት ከሐዋርያቱ ጋር መብላቱ
(ማቴ. 26፥17-25፤ ማር. 14፥12-21፤ ዮሐ. 13፥21-30)
7ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። 8ኢየሱስ “የፋሲካውን ራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ሲል ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው።
9እነርሱም “የፋሲካውን ራት የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት።
10እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማ ስትገቡ እነሆ፥ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ። 11የቤቱንም ጌታ መምህራችን፥ ‘ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው? ይልሃል’ በሉት። 12እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።” 13ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ሄደው፥ ሁሉ ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙ፤ የፋሲካውንም ራት በዚያ አዘጋጁ።
የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት
(ማቴ. 26፥26-30፤ ማር. 14፥22-26፤ 1ቆሮ. 11፥23-25)
14የእራት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። 15እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን የፋሲካ ራት ለመብላት እጅግ እመኝ ነበር፤ 16የዚህ ነገር እውነተኛ ምሥጢር በእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን የፋሲካ ራት ከቶ አልበላም እላችኋለሁ።”
17ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንካችሁ ይህንን ተካፈሉ፤ 18በእውነት እላችኋለሁ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከዚህ ከወይን ፍሬ የሚገኘውን መጠጥ አልጠጣም።”
19ቀጥሎም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ፤ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፤ ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ሰጣቸው። 20እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ ሰጣቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው። #ኤር. 31፥31-34።
21“ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ ከእኔ ጋር በማእድ ነው። #መዝ. 41፥9። 22የሰው ልጅ ስለ እርሱ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!”
23እነርሱም “ከእኛ መካከል ይህን ነገር የሚያደርግ የትኛው ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።
ከሁሉ የሚበልጥ ማነው?
24ቀጥሎም እነርሱ፥ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” እያሉ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። #ማቴ. 18፥1፤ ማር. 9፥34፤ ሉቃ. 9፥46። 25ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የዚህ ዓለም ነገሥታት በሕዝቡ ላይ ሥልጣን አላቸው፤ ገዢዎችም የሕዝቡ በጎ አድራጊዎች ይባላሉ፤ #ማቴ. 25፥27፤ ማር. 10፥42-44። 26እናንተ ግን እንደ እነርሱ ልትሆኑ አይገባም፤ ይልቅስ ከእናንተ መካከል ትልቅ የሆነ እንደ ትንሽ ይሁን፤ አለቃ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። #ማቴ. 23፥11፤ ማር. 9፥35። 27በማእድ ተቀምጦ ከሚመገበውና ቆሞ ከሚያገለግለው የትኛው ነው ትልቅ? ትልቅ የሚባለው በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። #ዮሐ. 13፥12-15። 28እናንተ በመከራዬ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ ቈይታችኋል። 29ስለዚህ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም እናንተን እሾማችኋለሁ። 30በመንግሥቴም በማእድ ተቀምጣችሁ ትበላላችሁ፤ ትጠጣላችሁ፤ በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።” #ማቴ. 19፥28።
ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ መናገሩ
(ማቴ. 26፥31-35፤ ማር. 14፥27-31፤ ዮሐ. 13፥36-38)
31ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ስምዖን! ስምዖን! እነሆ፥ ገበሬ ስንዴውን ከገለባ አበጥሮ እንደሚለይ እንዲሁም ሰይጣን እናንተን ሊያበጥራችሁ ፈለገ። 32ነገር ግን የአንተ እምነት እንዳይጠፋ እኔ ለአንተ እጸልያለሁ፤ እንደገና በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና።”
33ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ለእስራትም ሆነ ለሞት ከአንተ ጋር አብሬ ለመሄድ ዝግጁ ነኝ!” አለ።
34ኢየሱስ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ‘አላውቀውም’ ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው።
35ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የገንዘብ ቦርሳ፥ ከረጢት፥ ጫማም ሳትይዙ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። #ማቴ. 10፥9-10፤ ማር. 6፥8-9፤ ሉቃ. 9፥3፤ 10፥4።
እነርሱም “ምንም የጐደለብን ነገር አልነበረም” ሲሉ መለሱለት።
36ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን የገንዘብ ቦርሳም ሆነ ከረጢት ያለው ይያዝ፤ ሰይፍም የሌለው ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። 37ስለ እኔ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ስለሚገባው ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል በእኔ ላይ መፈጸም አለበት እላችኋለሁ።” #ኢሳ. 53፥12።
38ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ እዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ!” አሉት።
እርሱም “ይበቃል!” አላቸው።
ኢየሱስ በደብረ ዘይት መጸለዩ
(ማቴ. 26፥36-46፤ ማር. 14፥32-42)
39ኢየሱስ ከከተማ ወጥቶ እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረውት ሄዱ። 40እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው።
4141 ከዚህ በኋላ የድንጋይ ውርወራ ያኽል ከእነርሱ ራቅ ብሎ ሄደ፤ ተንበርክኮም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ 42“አባት ሆይ! ፈቃድህ ቢሆን ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” 43በዚያን ጊዜ የሚያበረታታው መልአክ ከሰማይ መጥቶ ታየው። 44ልቡም በጣም ተጨንቆ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር።
45ከጸሎቱ ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ ከሐዘን ብዛት የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና እንዲህ አላቸው፤ 46“ስለምን ትተኛላችሁ? ይልቅስ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ።”
የኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ
(ማቴ. 26፥47-56፤ ማር. 14፥43-50፤ ዮሐ. 18፥3-11)
47ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብዙ ሰዎች መጡ፤ መሪያቸው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ሊስመው ወደ ኢየሱስ ቀረበ። 48ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።
49ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት የነገሩን ሁኔታ ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉ። 50ከእነርሱም አንዱ የካህናት አለቃውን አገልጋይ በሰይፍ መታና ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ።
51ኢየሱስ ግን “ተው! እንደዚህ ያለ ነገር ደግመህ አታድርግ!” አለ፤ የሰውዬውንም ጆሮ ዳስሶ አዳነው።
52ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፥ የቤተ መቅደስ የዘብ አዛዦችንና የሕዝብ ሽማግሌዎችንም እንዲህ አላቸው፦ “እኔን እንደ ወንበዴ ልትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? 53በየቀኑ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር ስገኝ አልያዛችሁኝም ነበር፤ አሁን ግን የእናንተ ጊዜና የጨለማው ሥልጣን ጊዜ ነው።” #ሉቃ. 19፥47፤ 21፥37።
ጴጥሮስ ኢየሱስን መካዱ
(ማቴ. 26፥57-58፤69-75፤ ማር. 14፥53-54፤66-72፤ ዮሐ. 18፥12-18፤25-27)
54ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱትና ወደ ካህናት አለቃው ቤት አመጡት፤ ጴጥሮስም ራቅ ብሎ ይከተለው ነበር። 55ሰዎቹ በግቢው ውስጥ እሳት አቀጣጥለው በአንድነት ተቀምጠው ነበር። ጴጥሮስም መጥቶ አብሮ ተቀመጠ። 56ጴጥሮስ በእሳቱ አጠገብ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ በእሳቱ ብርሃን አየችው፤ ወደ እርሱ ትኲር ብላ ተመልክታም “ይህም ከኢየሱስ ጋር ነበር!” አለች። 57ጴጥሮስ ግን፥ “አንቺ ሴት! እኔ አላውቀውም!” ሲል ካደ። 58ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሌላ ሰው ጴጥሮስን አየውና “አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ!” አለው።
ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! አይደለሁም!” አለ።
59አንድ ሰዓት ያኽል ቈይቶም አንድ ሌላ ሰው ጴጥሮስን “ይህ ሰው ገሊላዊ ነውና በእርግጥ ከእርሱ ጋር ነበረ!” በማለት አጥብቆ ተናገረ። 60ጴጥሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም!” አለ። ይህን ሲናገር ሳለ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። 61በዚህ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ዞር ብሎ ጴጥሮስን አየው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” በማለት ጌታ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታወሰ። 62ወደ ውጪ ወጥቶም ምርር ብሎ አለቀሰ።
63በዚያን ጊዜ ኢየሱስን ይዘውት የነበሩ ሰዎች በእርሱ ላይ ያፌዙበትና ይደበድቡትም ነበር። 64ፊቱንም እየሸፈኑ፥ “ማን ነው የመታህ? ነቢይ ከሆንክ እስቲ ዕወቅ!” ይሉት ነበር። 65በእርሱም ላይ ብዙ ነገር እየተናገሩ ይሰድቡት ነበር።
ኢየሱስ ወደ ፍርድ ሸንጎ መወሰዱ
(ማቴ. 26፥59-66፤ ማር. 14፥55-64፤ ዮሐ. 18፥19-24)
66በነጋ ጊዜም የሕዝብ ሽማግሌዎች፥ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም ወደ ሸንጎአቸው አመጡት። 67እንዲህም አሉት፦ “እስቲ አንተ መሲሕ ከሆንክ ንገረን፤” እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ 68ጥያቄም ባቀርብላችሁ አትመልሱልኝም፤ 69ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ይቀመጣል።” 70ሁሉም በአንድነት “ታዲያ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አዎ፥ እናንተ እንዳላችሁት ነው” አላቸው። 71እነርሱም “እንግዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? እነሆ፥ ከአፉ የወጣውን ቃል እኛ ራሳችን ሰምተናል!” አሉ።
Tans Gekies:
የሉቃስ ወንጌል 22: አማ05
Kleurmerk
Deel
Kopieer
Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997