የሉቃስ ወንጌል 13
13
ንስሓ የማይገባ ሁሉ እንደሚጠፋ
1በዚያን ጊዜ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው፥ “የገሊላ ሰዎች መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ ጲላጦስ ገደላቸው፤ ደማቸውም ከመሥዋዕታቸው ጋር አደባለቀ” ሲሉ ነገሩት። 2ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ታዲያ፥ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ጥፋት የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ኃጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋልን? 3‘አይደለም፤ ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ’ እላችኋለሁ። 4በሰሊሆም ግንብ ተደርምሶባቸው ስለሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች ምን ታስባላችሁ? እነርሱ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የባሱ ኃጢአተኞች የነበሩ ይመስሉአችኋልን? 5አይደለም! ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ እላችኋለሁ።”
የማታፈራ የበለስ ዛፍ ምሳሌ
6ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን ተክሉ ቦታ ውስጥ የተተከለች አንዲት የበለስ ዛፍ ነበረችው፤ ከዚያች የበለስ ዛፍ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ቢሄድ ምንም ሳያገኝ ቀረ። 7ስለዚህ አትክልተኛውን ‘እነሆ፥ ከዚህች የበለስ ዛፍ ፍሬ ለማግኘት ሦስት ዓመት ሙሉ ተመላለስኩ፤ ግን ምንም ፍሬ አላገኘሁባትም፤ አሁንስ ቊረጣት! ስለምንስ መሬቱን ታበላሻለች?’ አለው። 8አትክልተኛው ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታዬ ሆይ! እስቲ ለዚህ ዓመት ደግሞ ተዋት፤ ዙሪያዋን ኰትኲቼ ማዳበሪያ አደርግላታለሁ፤ 9ለመጪው ዓመት ፍሬ ብትሰጥ መልካም ነው፤ አለበለዚያ ግን ትቈረጣለች።’ ”
ኢየሱስ አንዲት ጀርባዋ የጐበጠ ሴት በሰንበት ቀን መፈወሱ
10ኢየሱስ በሰንበት ቀን ከምኲራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር፤ 11ከዚያም ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ ጀርባዋን ያጐበጣት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርስዋ ወገብዋ በመጒበጡ ቀና ለማለት በፍጹም አትችልም ነበር። 12ኢየሱስ ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት ከበሽታሽ ተፈውሰሻል!” አላት። 13እጆቹን ጫነባት፤ ወዲያውም ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።
14ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ የምኲራቡ አለቃ ተቈጣና ለሕዝቡ፦ “በሳምንት ውስጥ ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ በእነዚህ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ፤ በሰንበት ቀን ግን አይሆንም” ብሎ ተናገረ። #ዘፀ. 20፥9-10፤ ዘዳ. 5፥13-14።
15ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተስ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሬውን ከተዘጋበት አውጥቶ፥ ወይም አህያውን ከታሰረበት ፈቶ ውሃ ወደሚያጠጣበት ቦታ ይወስደው የለምን? 16እነሆ፥ የአብርሃም ዘር የሆነች ይህች ሴት ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትሠቃይ ኖራለች፤ ታዲያ፥ እርስዋ ታስራ ከምትሠቃይበት በሽታ በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?” 17በዚህም ንግግሩ ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ አሳፈራቸው፤ ሕዝቡ ግን ኢየሱስ ባደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ተደሰተ።
የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ
(ማቴ. 13፥31-32፤ ማር. 4፥30-32)
18ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምን ትመሰላለች? ወይስ ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ? 19አንድ ሰው በአትክልቱ ውስጥ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ አድጋ ዛፍ ሆነች፤ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠሩ።”
የእርሾው ምሳሌ
(ማቴ. 13፥33)
20ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ? 21የእግዚአብሔር መንግሥት፥ አንዲት ሴት ሊጡ በሙሉ እንዲቦካ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች።”
ስለ ጠባብዋ በር
(ማቴ. 7፥13-14፤21-23)
22ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሳለ በየከተማውና በየገጠሩ እያስተማረ ያልፍ ነበር። 23በዚያን ጊዜ አንድ ሰው፥ “ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ሰዎች ናቸውን?” ሲል ጠየቀው፤
ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ 24“በጠባብዋ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ በዚህች በር መግባት የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው፤ ነገር ግን መግባት አይችሉም እላችኋለሁ። 25የቤቱ ጌታ ተነሥቶ በሩን ይዘጋዋል፤ እናንተም በደጅ ቆማችሁ በሩን በማንኳኳት፥ ‘ጌታ ሆይ! እባክህ ክፈትልን!’ ማለት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም ‘ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም!’ ሲል ይመልስላችኋል። 26በዚያን ጊዜ እናንተ፥ ‘ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ አብረን ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል’ ትሉታላችሁ። 27እርሱም እንደገና ‘ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም፤ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ከእኔ ራቁ!’ ይላችኋል። #መዝ. 6፥8። 28አብርሃምን፥ ይስሐቅን፥ ያዕቆብን ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ታዩአቸዋላችሁ፤ እናንተ ግን በውጪ ተጥላችሁ ስትቀሩ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይደርስባችኋል። #ማቴ. 22፥13፤ 25፥30። 29ብዙ ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር መንግሥትም በማእድ ይቀመጣሉ። #ማቴ. 8፥11-12። 30ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።” #ማቴ. 19፥30፤ 20፥16፤ ማር. 10፥31።
ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ማልቀሱ
(ማቴ. 23፥37-39)
31በዚያን ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ወጥተህ ሂድ” አሉት።
32ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ለዚያ ቀበሮ፦ ‘ዛሬና ነገ አጋንንትን አስወጣለሁ፤ በሽተኞችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛው ቀንም ሥራዬን እጨርሳለሁ’ ይላል በሉት። 33ይሁን እንጂ ዛሬና ነገ ከነገ ወዲያም መንገዴን ወደ ኢየሩሳሌም መቀጠል አለብኝ፤ ነቢይ ከኢየሩሳሌም በቀር በሌላ ቦታ መሞት አይገባውም።
34“ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፥ ወደ አንቺ የተላኩትንም መልእክተኞች በድንጋይ የምትወግሪ፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ፥ እኔም ስንት ጊዜ ልጆችሽን መሰብሰብ ፈለግኹ! አንቺና ሕዝብሽ ግን እምቢ አላችሁ። 35ስለዚህ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀራል፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከቶ አታዩኝም።” #መዝ. 118፥26፤ ኤር. 22፥5።
Tans Gekies:
የሉቃስ ወንጌል 13: አማ05
Kleurmerk
Deel
Kopieer
Wil jy jou kleurmerke oor al jou toestelle gestoor hê? Teken in of teken aan
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997