YouVersion Logo
Search Icon

ዘፍጥረት 15

15
እግዚአብሔር ለአብራም የገባው ኪዳን
1ከዚህም በኋላ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤
“አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤
እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤#15፥1 ወይም ገዥ
ታላቅ ዋጋህም#15፥1 ወይም ዋጋህም እጅግ ታላቅ ይሆናል እኔው ነኝ።”
2አብራምም፣ “እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለሆንሁ፣ የቤቴ ወራሽ#15፥2 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም አይታወቅም። የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” አለው። 3“አንተ ልጆች ስላልሰጠኸኝ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም።”
4በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል።” 5ወደ ውጭም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቍጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቍጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው።
6አብራም እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት።
7ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔ ነኝ” አለው።
8አብራምም፣ “እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ።
9 እግዚአብሔርም (ያህዌ) “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ፣ በተጨማሪም አንድ ዋኖስና አንድ ርግብ አብረህ አቅርብልኝ” አለው።
10አብራምም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቈርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ፣ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጠ፤ ዋኖሷንና ርግቧን ግን ለሁለት አልከፈላቸውም። 11አሞሮችም ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራም ግን አባረራቸው።
12ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት። 13እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር ስደተኛ እንደሚሆን በርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። 14ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እፈርድበታለሁ፤ ከዚያም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ። 15አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ፤ 16በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፤ የአሞራውያን ኀጢአት ገና ጽዋው አልሞላምና።”
17ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ። 18በዚያ ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብፅ ወንዝ#15፥18 ወይም ደረቅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ 19የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄኔዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ 20የኬጢያውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የራፋይምን፣ 21የአሞራውያንን፣ የከነዓናውያንን፣ የጌርጌሳውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር ነው።”

Currently Selected:

ዘፍጥረት 15: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy