ኦሪት ዘፍጥረት 21

21
የይስሐቅ መወለድ
1ስለዚህ እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት ለሣራ መልካም በማድረግ የገባውን ቃል ኪዳን ፈጸመላት። 2ስለዚህም ፀንሳ በእርጅናው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ልጁም የተወለደው “በዚህ ጊዜ ይወለዳል” ብሎ እግዚአብሔር በተናገረበት ጊዜ ነው። #ዕብ. 11፥11። 3አብርሃም ሚስቱ ሣራ የወለደችለትን ልጅ “ይስሐቅ” ብሎ ስም አወጣለት፤ 4ይስሐቅ ከተወለደ ከስምንት ቀን በኋላ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አብርሃም ገረዘው። #ዘፍ. 17፥12፤ ሐ.ሥ. 7፥8። 5ይስሐቅ በተወለደ ጊዜ አብርሃም መቶ ዓመት ሆኖት ነበር። 6ሣራ “እግዚአብሔር ደስታና ሳቅ አመጣልኝ፤ ስለዚህ ይህን ነገር የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋር ይስቃል” አለች። 7ቀጥላም “ ‘ሣራ ለአብርሃም ልጅ ወልዳ ታጠባለች’ ብሎ የሚናገር ከቶ ማን ነበር? አሁን ግን እነሆ በእርጅናው ዘመን ወንድ ልጅ ወለድኩለት” አለች።
8ልጁም አድጎ ጡት መጥባት ተወ፤ ጡት ባስጣሉበትም ቀን አብርሃም ታላቅ ግብዣ አደረገ።
የአጋርና የእስማኤል መባረር
9ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል ከዕለታት አንድ ቀን ሣራ ከልጅዋ ከይስሐቅ ጋር ሲጫወት አየችው፤ 10ሣራም አብርሃምን “ይህችን አገልጋይ ከነልጅዋ ወዲያ አባርልኝ፤ የዚህች አገልጋይ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አብሮ መውረስ አይገባውም” አለችው። #ገላ. 4፥29-30። 11አብርሃምም ስለ ልጁ ስለ እስማኤል በብርቱ ተጨነቀ፤ 12እግዚአብሔር ግን አብርሃምን “ስለ ልጁና ስለ አገልጋይቱ ስለ አጋር አትጨነቅ፤ ዘር የሚወጣልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ ሣራ የምትልህን ሁሉ አድርግ፤ #ሮም 9፥7፤ ዕብ. 11፥18። 13የአገልጋይቱም ልጅ የአንተ ልጅ ስለ ሆነ ታላቅ ሕዝብ እስኪሆን ድረስ ዘሩን አበዛለሁ” አለው።
14በማግስቱ ጠዋት አብርሃም በማለዳ ተነሣ፤ ጥቂት ምግብ፥ ውሃም በአቁማዳ ሞልቶ ለአጋር ሰጣት፤ ልጁንም በጀርባዋ አሳዝሎ ከቤት አስወጣት፤ እርስዋም ከዚያ ወጥታ በቤርሳቤህ በረሓ ትንከራተት ጀመር። 15በአቁማዳ የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ ልጁን በቊጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው፤ 16እርስዋም “ልጄ ሲሞት ማየት አልፈልግም” በማለት ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያኽል ርቃ ተቀመጠች፤ እዚያም ሆና ታለቅስ ጀመር።
17እግዚአብሔርም ልጁ ምርር ብሎ ሲያለቅስ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን “አጋር ሆይ፤ የምትጨነቂበት ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር የልጁን ለቅሶ ሰምቶአልና አይዞሽ አትፍሪ፤ 18ተነሺ፤ ሂጂና ልጁን አንሥተሽ ዕቀፊው የእርሱንም ዘር አበዛለሁ፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ” አላት። 19በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ዐይኖችዋን ከፈተላትና አንድ የውሃ ጒድጓድ አየች፤ ሄዳም በአቁማዳው ውሃ ሞላች፤ ለልጅዋም አጠጣችው። 20ልጁ እያደገ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበር፤ በፋራንም በረሓ ኖረ፤ ቀስት በመወርወርም የታወቀ አዳኝ ሆነ። 21እናቱም ከአንዲት ግብጻዊት ጋር አጋባችው።
በአብርሃምና በአቤሜሌክ መካከል የተደረገ ስምምነት
22በዚያን ጊዜ አቤሜሌክ ከሠራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር ሄደና አብርሃምን “በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ #ዘፍ. 26፥26። 23እኔንም ሆነ ልጆቼን ወይም ዘሮቼን በማታለል እንዳትበድል እዚህ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ፤ እኔ ለአንተ ታማኝነትን አሳይቻለሁ፤ አንተም ለእኔና ለዚህች በመጻተኛነት ለምትኖርባት አገር ታማኝነትን እንደምታሳይ ማልልኝ” አለው።
24አብርሃምም “እሺ እምላለሁ” አለው።
25አብርሃም፥ የአቤሜሌክ አገልጋዮች ስለ ወሰዱበት የውሃ ጒድጓድ ለአቢሜሌክ አቤቱታ አቀረበ። 26አቤሜሌክም “ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ አላውቅም፤ አንተም አልነገርከኝም፤ ይህን ነገር ገና ዛሬ መስማቴ ነው” አለው፤ 27ከዚህ በኋላ አብርሃም ብዙ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ በዚያን ቀን ሁለቱም የስምምነት መሐላ አደረጉ። 28በዚያን ጊዜ አብርሃም ሰባት ሴት በጎችን ከመንጋው ለየ፤ 29አቤሜሌክም “እነዚህን ሰባት ሴት በጎች ለይተህ ያቆምካቸው ለምንድን ነው?” አለው።
30አብርሃምም “እነዚህን ሰባት ቄቦች ተቀበለኝ፤ እነርሱን ከተቀበልከኝ ይህን ጒድጓድ የቈፈርኩ እኔ መሆኔን ታረጋግጣለህ” አለው። 31ሁለቱ ተማምለው የተስማሙበት ስፍራ በመሆኑ የዚያ ቦታ ስም ቤርሳቤህ ተባለ። #21፥31 ቤርሳቤህ፦ በዕብራይስጥ “በኤር ሼባዕ” ሲሆን “የሰባት ወይም የመሐላ የውሃ ጒድጓድ” ማለት ነው።
32ይህን ስምምነት በቤርሳቤህ ካደረጉ በኋላ አቤሜሌክና የሠራዊቱ አለቃ ፊኮል ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ፤ 33ከዚህ በኋላ አብርሃም በቤርሳቤህ የታማሪስክ ዛፍ ተከለና ለዘለዓለማዊው አምላክ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ #21፥33 ታማሪስክ፦ ቁመቱ አጠር ያለና ከተምር የተለየ ዛፍ ነው። 34አብርሃም በፍልስጥኤም ምድር በእንግድነት ለረዥም ጊዜ ኖረ።

高亮显示

分享

复制

None

想要在所有设备上保存你的高亮显示吗? 注册或登录