ኦሪት ዘፍጥረት 13

13
አብራምና ሎጥ ተለያዩ
1አብራም ሚስቱንና ያለውን ሀብት ሁሉ ይዞ ከግብጽ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። 2አብራም ብዙ እንስሶች፥ ብዙ ብርና ወርቅ ያለው ሀብታም ሰው ነበረ።
3ከኔጌብ ተነሥቶም ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ወደ ቤትኤል አመራ፤ በቤትኤልና በዐይ መካከል ወዳለውም ስፍራ ደረሰ፤ ይህም ስፍራ ከዚህ በፊት ድንኳን ተክሎ የሰፈረበትና፥ 4መሠዊያም ሠርቶበት የነበረው ነው፤ እዚያም አብርሃም እግዚአብሔርን አመለከ።
5ከአብራም ጋር ይጓዝ የነበረው ሎጥም በበኩሉ፥ ብዙ በጎች፥ ፍየሎችና ከብቶች፥ ድንኳኖችም ነበሩት። 6ከብቶቻቸውን በአንድነት የሚያሰማሩበት በቂ የግጦሽ ቦታ ስላልነበረና አብራምና ሎጥ ብዙ የከብት መንጋ ስለ ነበራቸው አብረው ለመኖር አልቻሉም፤ 7ከዚህም የተነሣ በአብራም እረኞችና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተነሣ፤ በዚያን ዘመን የዚያች ምድር ነዋሪዎች ከነዓናውያንና ፈሪዛውያን ነበሩ።
8ከዚህ በኋላ አብራም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማች ስለ ሆንን በእኔና በአንተ መካከል እንዲሁም በእኔ እረኞችና በአንተ እረኞች መካከል ጠብ ሊነሣ አይገባም፤ 9ምድሪቱ ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ተለይተህ ሂድ፤ አንተ ወደ ግራ ብትሄድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ ወይም አንተ ወደ ቀኝ ብትሄድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።”
10ሎጥ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ የዮርዳኖስ ሸለቆ እስከ ጾዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት ወይም እንደ ግብጽ ምድር ውሃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ ይህን የተመለከተው እግዚአብሔር የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነበር። #ዘፍ. 2፥10። 11ስለዚህ ሎጥ መላውን የዮርዳኖስን ሸለቆ ለራሱ መረጠና ወደ ምሥራቅ ሄደ፤ ሁለቱ የተለያዩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ 12አብራም በከነዓን ኖረ፤ ሎጥ ግን በሸለቆው ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል ተቀመጠ፤ በሰዶምም አጠገብ ድንኳኑን ተከለ፤ 13በዚያን ዘመን የሰዶም ሰዎች እጅግ ክፉዎችና እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ኃጢአተኞች ነበሩ።
የአብራም ወደ ኬብሮን መሄድ
14ሎጥ ከሄደ በኋላ እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ካለህበት ስፍራ ሆነህ ወደ ሰሜን፥ ወደ ደቡብ፥ ወደ ምሥራቅና ምዕራብ ተመልከት፤ 15ይህን የምታየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ እሰጣችኋለሁ፤ ለዘለዓለምም የእናንተ ይሆናል፤ #ሐ.ሥ. 7፥5። 16ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ፤ የምድር አሸዋ ሊቈጠር እንደማይቻል ሁሉ የአንተም ዘር እንዲሁ ሊቈጠር የማይቻል ይሆናል። 17ተነሥተህ በምድሪቱ ስፋትና ርዝመት ሂድ፤ ሁሉንም ለአንተ እሰጥሃለሁ።”
18ስለዚህ አብራም ድንኳኑን ነቅሎ በኬብሮን የመምሬ የተቀደሱ የወርካ ዛፎች ወደአሉበት ስፍራ ለመኖር ሄደ፤ እዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።

高亮显示

分享

复制

None

想要在所有设备上保存你的高亮显示吗? 注册或登录